ግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ ()

በእንተ ማርያም መሐረነ ክርስቶስ ()

ኪርያላይሶን ()

ኦ....! አምላክ ()
ኦ.....! ክርስቶስ ()

ያድነን እመአቱ ይሰውረነ በምህረቱ ()
በእንተ ማርያም ወላዲቱ ()
ስምአነ አምላክነ ወመድኃኒነ ()

 

 

እንደ ቸርነትህ አቤቱ ማረን (፪)
እንደምህረትህም ይቅርታን ስጠን (፪)
ከኃጢአቴም አንጻኝ ከክፉ በደሌ (፪)
ለዚያች ክፉ ኃጢአት እንዳልሆናት ሎሌ (፪)
እኔስ አበሳዬ በደሌን ሳውቀው (፪)
ከቶ የሚያድነኝ ቸርነትህ ነው (፪)
አንተን ብቻ በደልኩ ክፉም አደረግሁ (፪)
አሁን ይቅር በለኝ ከፊትህ ወደቅሁ (፪)
ከፊትህ ወድቄ ስለምን አንተን (፪)
መውደቄን ተመልከት አምላከ ብርሃን (፪)
አሁን ትባርክ ዘንድ ሃገራችንን ሃይማኖታችንን
ጌታ ሆይ ላክልን መንፈስ ቅዱስን ጰራቅሊጦስን
አሁን ትቀበል ዘንድ ጸሎታችንን ምህላችንን
ጌታ ሆይ ላክልን ቅዱስ ሚካኤልን ቅዱስ ገብርኤልን

 

 

የዘወትር ጸሎት ውዳሴ ማርያም

 

በጌታዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ትዕምርተ መስቀል ፊቴንና መላ ሰውነቴን ሶስት ጊዜ አማትባለሁ።
እግዚአብሔርን ስለማምን አንድ አምላክ በሆኑ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ልዩ ክብር ጽሩይ በሆኑ በሶስትነት ወይም በሥላሴ እያመንኩና እየተማፀንኩ ጠላቴን ሰይጣንን እክዳለሁ፣ በዚች በእናቴ በቤተ ክርስቲያን ፊት ቁሜ እክድሃለሁ፣ ለዚህም ምስክሬ ማርያም ናት በዚህም ዓለም በወዲያኛውም ዓለም እስዋን አምባ መጠጊያ አድርጌ እክድሃለሁ።


አቤቱ እናመሰግንሃለን አቤቱ እናከብርሃለን አቤቱ እንገዛልሃለን አቤቱ ቅዱስ ስምህን እናመሰግናለን ጉልበት ሁሉ የሚሰግድልህ አቤቱ እንሰግድልሃለን አንደበት ሁሉ ላንተ ይገዛል የአምላኮች አምላክ የጌቶ ጌታ የንጉሦች ንጉሥ አንተ ነህ። የስጋም የነፍስም ፈጣሪ አንተ ነህ። እናንተስ በምትፀልዩበት ጊዜ እንዲህ ብላችሁ ፀልዩ ብሎ ቅዱስ ልጅህ እንዳስተማረን እንጠራሃለን።


አባታችን ሆይ በሰማይ የምትኖር ስምህ ይቀደስ መንግስትህ ትምጣ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን፣ የዕለት እንጀራችንን ስጠን ለዛሬ በደላችንንም ይቅር በለን እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል። አቤቱ ወደ ፈተናም አታግባን ከክፉ ሁሉ አድነን እንጂ መንግሥት ያንተ ናትና ኃይል ክብር ምስጋና ለዘላለሙ አሜን።


እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ ሰላም እልሻለሁ በሃሳብሽ ድንግል ነሽ በሥጋሽም ድንግል ነሽ። የአሸናፊ የእግዚአብሔር እናት ሆይ ሰላምታ ላንቺ ይገባል። ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ አንቺ የተባረክሽ ነሽ የማህጸንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። ጸጋን የተሞላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነውና ከተወደደው ልጅሽ ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ይቅርታንና ምሕረትን ለምኝልን ኃጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን።

 

ሁሉን የፈጠረ አንድ አምላክ በሚሆን በእግዚአብሔር አብ እናምናለን። ሰማይና ምድርን  የሚታየውንና የማይታየውን የፈጠረ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን። ዓለም ሳይፈጠር ከርሱ ጋር በነበረ የአብ አንድ ልጅ በሚሆን በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን። ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ የተፈጠረ ያይደለ የተወለደ በመለኮቱ ከአብ ጋር የሚተካከል ሁሉ በእርሱ የሆነ ያለ እርሱ ግን ምንም ምን የሆነ የለም በሰማይም ካለው በምድርም ካለው ስለኛ ስለ ሰዎች ስለ መዳናችን ከሰማይ ወረደ በመንፈስ ቅዱስ ግብር የተነሳ ከቅድስት ድንግል ማርያም ፍጽሞ ሰው ሆነ፣ ሰው ሆኖ በጴንጤናዊ በጲላጦስ ዘመን ስለ እኛ መከራን ተቀበለ፣ ታመመ ሞተ ተቀበረ በሶስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሳ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተጻፈ በክብር በምስጋና ወደ ሠማይ ዐረገ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ ዳግመኛም በሕያዋንና በሙታን ይፈርድ ዘንድ በምስጋና ይመጣል። ለመንግሥቱም ፍፃሜ የለውም። ጌታ ማሕየዊ በሚሆን ከአብ በሰረጸ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን እንሰግድለታለን እናመሰግነዋለን፣  ከአብና ከወልድ ጋራ በነቢያት የተናገረ ነው። ከሁሉም በላይ በምትሆን ሐዋርያት በሰርዋት በአንዲት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን። ኃጢያት በሚሰረይባት በአንዲት ጥምቀት እናምናለን የሙታንንም መነሳት ተስፋ እናደርጋለን የሚመጣውንም ሕይወት ለዘላለሙ አሜን፣


፮. አሸናፊ እግዚአብሔር ሆይ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ተብለህ ትመሠገናለህ። ምስጋናህም በሰማይ በምድር የመላ ነው። ክርስቶስ ሆይ ላንተ እንሰግድልሃለን ሰማያዊ ከሚሆን ከቸር አባትህ ጋር አዳኝ ከሚሆን ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አዳኝ እንሰግድልሃለን ወደዚህ አለም መጥተህ አድነኸናልና።


፯. ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አንዲት ስግደት እሰግዳለሁ ፫ጊዜ በል አንድ ሲሆኑ ሦስት ሦስት ሲሆኑ አንድ በአካል ሦስት ሲሆኑ በመለኮት አንድ ለሚሆኑ አምላክ እሰግዳለሁ። አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ለድንግል ማርያምም እሰግዳለሁ። ዓለምን ሁሉ ለማዳን ሲል እየሱስ ክርስቶስ ለተሰቀለበት መስቀል እሰግዳለሁ። መስቀል ኃይላችን ነው። ኃይላችን መስቀል ነው የሚያፀናን መስቀል ነው፡ መስቀል ቤዛችን ነው፡ መስቀል የነፍሳችን መዳኛ ነው አይሁድ ይክዱታል እኛ ግን እናምነዋለን ያመነውም እኛም በመስቀሉ እንድናለን ድነናልም።


፰. ለአብ ምስጋና ይገባል ለወልድም ምስጋና ይገባል። ለመንፈስ ቅዱስም ምስጋና ይገባል ፫ጊዜ በል።
አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ለድንግል ማርያም ምስጋና ይገባል።ለኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልም ምስጋና ይገባል። ክርስቶስ በቸርነቱ ያስበን ዘንድ ዳግመኛም በመጣ ጊዜ እንድዳያሳፍረን ስሙን ለማመስገን ያበቃን ዘንድ እመቤታችን ፀሎታችንን አሳርጊልን። ኃጢያታችንንም አስተሥርዪልን በጌትልችን መንበር ፊት ፀሎታችንን አሳርጊልን ይህንን ኅብስት ላበላን ይህንንም ጽዋ ላጠጣን ምግባችንና ልብሳችንንም ላዘጋጀልን ኃጢያታችንንም ሁሉ ለታገሰልን ክቡር ደሙን ቅዱስ ስጋውን ለሰጠን እስከዚህችም ሰዓት ላደረሰን ለእሱ ለልዑል እግዚአብሔር ፍፁም ምስጋና ይገባል ለወለደችው ለድንግልም ምስጋና ይገባል። ለክቡር መስቀሉም ምስጋና ይገባል። እግዚአብሔር ስሙ ፈፅሞ ይመሰገን ዘንድ ዘወትር በየጊዜያቱ በየሰዓቱ ምስጋና ይገባል።


፱. እናታችን ማርያም ሆይ ሰላም ላንቺ ይሁን እያልን እንሰግድልሻለን እንማልድሻለን ከአዳኝ አውሬ ታድኝን ዘንድ ተማጽነንብሻል ስለ እናትሽ ስለ ሐና ብለሽ ስለ አባትሽ ስለ እያቄም ብለሽ ድንግል ማኅበራችንን ዛሬ ባርኪልን።


፲. አምላክን በድንግልና የወለደች የእመቤታችን የማርያም ፀሎት ሉቃ ፩፡፵፮-፶፬
ማርያምም አለች ነፍሴ እግዚአብሔርን ታላቅ ታደርገዋለች መንፈሴም በመድሐኒቴ በእግዚአብሔር ደስ ይላታል። የባሪያይቱን መዋረድ አይቷልና እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ያመሰግኑኛል። እርሱ ብርቱ የሚሆን ታላቅ ስራን ለእኔ አድርጉዋልና። ስሙም ቅዱስ ነው። ለሚፈሩትም ምሕረቱ ለልጅ ልጅ ነው። ኃይልን በክንዱ አደረገ። በልባቸው አሳብ የሚኮሩ ትዕቢተኞችን በታተናቸው ብርቱዎችንም ከዙፋናቸው አዋረዳቸው የተዋረዱትንም ከፍ ከፍ አደረጋቸው። የተራቡትንም በቸርነቱ አጠገባቸው ባለጠጎችንም ባዶ እጃቸውን ሰደዳቸው ምሕረቱን እንዲያስብ እስራኤል ባሪያውን ተቀበለ። ለአባቶቻችን ለአብርሃምና ለዘሩም እስከ ዘለዓለም ድረስ እንደተናገረው።

 

የእሁድ ውዳሴ ማርያም

 

ይዌድስዋ መላእክት


መላእክት ማርያምን በመንጦላት ውስጥ ያመሰግኗታል፤ ሐዳስ ጣዕዋ ላንቺ ምስጋና ይገባሻል ይላሉ። መልአክ ማርያምን ቃልን ተቀበይው አላት ካንቺ ዘንድ ይመጣልና በማኅፀንሽም ያድራል እንዴት ከድሀ ቤት አደረ እንደ ምስኪን ከሰማያት ወርዶ የርስዋን ባሕርይ ባሕርይ አድርጎ ተወለደ።

 

በ 6ኛው ወር ገብርኤል መልአክ ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ ተላክ ካንዲት አገር ናዝሬት ገሊላ ከምትባል ለዮሴፍ እጮኛ ከሆነች ከድንግል ዘንድ። የዚች የድንግል ስሟ ማርያም ነው መልአኩ ወደ እርስዋ ገብቶ እንዲህ አላት ደስታ ይገባሻል እግዚአብሔር ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነሥቶ ካንቺ ሰው ሆኗልና ከሴቶች ይልቅ አንቺ ብርክት ነሽ ...ከቃሉ አነጋገር አይታ ደነገጠች እንዲህም አለች እንዲህ ያለ የምስጋና እጅ መንሻ ይደረግልኛል? መልአክ እንዲህ አላት ማርያም ሆይ አትፍሪ ከእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አገኝተሻልና እነሆ ትፅንሻለን ትወልጃልሽ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ እርሱም ታላቅ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል እግዚአብሔር አምላክም የዳዊት ያባቱን ዙፋን ይሰጠዋል እርሱም በያዕቆብ ወገን ለዘላለሙ ይነግሳል መንግስቱም አያልፍም፤ ማርያምም መልአኩን እንዲህ አለችው ይህ ነገር እንደምን ይሆንልኛል እንዘ ኢየአምር ብእሴ መልአኩም እንዲህ አላት፤ መንፈስ ቅዱስ ይጠብቅሻል የሉዑል ኃይሉም ያድርብሻል ይህ የሚወልደው ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ ነው እነሆ ኤልሣቤጥ ካንቺ ወገን የምትሆን ከሸመገለች ካረጀች በኋላ ፀንሰች ልጅም አገኘች እነሆ ይህ ስድስት ወር ሆነ መካን ሲሏት ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና ማርያምም መልአኩን እንደ ቃልህ ይደረግልኝ እኔ ለእግዚአብሔር ባሪያው ነኝ አለቸው።

 

መልአኩ ገብርኤል ማርያም ድንግል ላንቺ ክብር ምስጋና ይገባሻል አላት። ወላዲተ አምላክ ምስጋና ይገባሻል ቅድስት ነሽና ምስጋና ይገባሻል የመለኮት ምደሪያ ነሽና ምስጋና ይገባሻል የተሸለምሽ ድንኳን ነሽና ምስጋና ይገባሻል የመላእክት እኅት የሕዝቡ ሁሉ እናት ነሽና ምስጋና ይገባሻል የሁሉ እመቤት ማርያም ምስጋና ይጋባሻል የሁሉ ፍቅረኛ ማርያም ምስጋና ይገባሻል ልዑል ማደሪያው ትሆኝ ዘንድ መርጦሻልና ምስጋና ይገባሻል በወርቅ የተሸለምሽ የርግብ ክንፍ በብር ያጌጥሽ ምስጋና ይገባሻል ጎኖችሽ በወርቅ አመልማሎ የተሸለሙ ላንቺ ምስጋና ይገባሻል። የምሥራቅ ደጃፍ የብርሃን እናቱ ላንቺ ምስጋና ይገባሻል ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበሪ ክብርሽ ከአድባራቱ ሁሉ ከፍ ከፍ ያለ አንቺ ምስጋና ይገባሻል ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበሪ ክብርሽ ከአድባራቱ ሁሉ ከፍ ከፍ ያለ ላንቺ ምስጋና ይገባሻል። ማርያም ሆይ ከተመረጡ የተመረጥሽ ከተከበሩ ላንቺ ምስጋና ይገባሻል ከጌታችን ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ለምኝልን ያድነን ዘንድ ከአባቱ ምስጋና ከስቅዱሳን መላእክቶቹ ጋር በመጣ ጊዜ ጻድቅንን በቀኙ ኃጥአንን በግራው ባቆመ ጊዜ እኛን ከሰማዕት እንጢፋኖስ ከመጥምኩ ዮሐንስ ጋር ከሁሉ ቅዱሳን ከሰማዕታት ጋር ያቆመን ዘንድ ለምኝልን ለዓለመ ዓለም ለዘለዓለሙ ይቅር ይበለን።