ወላዲተ አምላክ በኦርቶዶክስ ትውፊት

ክፍል ሦስት

(ሐ) ጽድቅን ለተራበ ትውልድ የሕይወትን መና የመገበች የሕያዋን ሁሉ እናት (የድኅነታችን መሠረት) በመሆኗ

 

በዚህ በሦስተኛው ክፍል ስለ ድንግል ማርያም ስንናገር ከንጽሕናዋ  ቅድስናዋ በተጨማሪ አብልጠን ትኩረት የምንሰጠው  ከድኅነተ-ዓለም ጋራ በተገናኙ መሠረታዊ ነገሮች ላይ ነው። ጥንቱን የሰው ዘር ሲፈጠር ፈጣሪውን እያስታወሰ በመታዘዝ እንዲኖር ከተሰጡት ሕጎች አንዱ እንዳይበላ የተከለከለውን ነገር ጠብቆ መኖር ነበር። ሆኖም አዳም ይህን ሕግ ጠብቆ መኖር ስለተሳነው በመብል ምክንያት ወደቀ። እናም የሰው ውድቀት ያሳዘነው ርኅሩኅ አማላካችን በመብል የገባውን ኃጢአት በመብል መደምሰስ ይቻል ዘንድ ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ በለበሰው ሥጋው ራሱን የሚበላ መስዋዕት አድርጎ አቀረበ። ይህም ሥጋ ከላይ ይዞት የመጣ ሳይሆን ከድንግል ማርያም የነሳው ነው። "የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም" (ዕብ 2:16) ሲል ቅዱስ ጳውሎስ እንደገለጸው። በዚህም ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ሕይወትን አገኝተናል። "ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ" (ዮሐ 6፡56) ብሏልና። ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬም ድንግል ማርያም በሰው ድኅነት ላይ ያላትን ቦታ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፣ "አንቲ ውዕቱ መሶበ ወርቅ ንጹሕ እንተ ውስቴታ መና ኅቡዕ" - "መና ያለብሽ መሶበ ወርቅ አንቺ ነሽ (ዘፀ. 16፡33)። ይኸውም መና የተባለው ከሰማይ የወረደና ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅፀንሽ የተሸከምሽው ልጅሽ ነው። እርሱም “አበዊክሙሰ መና በልዑ በገዳም ወሞቱ" - "አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ፤ ሞቱም” እንዳለው ያይደለ፤ ይልቁንም ለሰው ሁሉ ሕይወትን የሚያድል ሕብስት ነው (ዮሐ. 6፡50) ብሏል። ስለዚህ ድንግል ማርያምን የሕያዋን ሁሉ ባለውለታ በሰማይና በምድር ያሉ ምዕመናን እናት ተብላ ትጠራለች።

·  320-403 የነበረው ግሪካዊ ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ እንዲህ ይላል፣ "እርግጥ ነው በምድር ላይ ያለ ትውልድ ሁሉ ከሄዋን የተወለደ ነው፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን እውነተኛ ሕይወት የተገኘው ከድንግል ማርያም ነው፤ ምክንያቱም ሕያው የሆነውን ልጇን በመውለዷ የሕያዋን ሁሉ እናት ሆናለችና"።

·  በ354 ዓ.ም. የተወልደው ኦገስቲን የተባለ የላቲን ክርስቲያኖች አባት እንዲህ ብሏል፣ "የሰው ሁሉ ሰብሳቢ (ፈጣሪ) እናት እሱን በሥጋ በመውለድ በመንፈስ የዚህ መለኮታዊ አካል አባላት ለሆኑ ሁሉ እናት ሆነች"። 

ስለዚህ ቅድስት ድንግል ማርያምን የምናከብራት ለድኅነታችን ስለፈጸመችው በቃላት የማይገለጽ ውለታ ብቻ ሳይሆን ሄዋን ለአዳም ዘር ሁሉ እናት እንደሆነች እርሷም በክርስቶስ ለምናምን ሁሉ እናት ትሆን ዘንድ በዮሐንስ አማካኝነት "እናትህ እነኋት" (ዮሐ 19፡27) ተብላ በአደራነት ስለተሰጠችን ጭምር ነው። በዚያ በጭንቅና በመከራ ቀን ቅዱስ ዮሐንስ በአደራነት ተቀብሎ ወደ ቤቱ ወስዶ እስከ ዕለተ እረፍቷ በክብር ጠበቃት። ስለዚህ የአምላክ እናት የእኛም እናታችን በመሆኗ እንደ ዮሐንስ ባለ አደራ መሆናችንን ተገንዝበን ስዕሏን በቤታችን ፍቅሯን በልባችን ስለን ልንኖር ይገባል።

 

(መ) የጠላታችንን ራስ እንቀጠቅጥበት ዘንድ በትርን ያቀበለችን ብልህ ሴት በመሆኗ

የአዳምን ውድቀት ተከትሎ ጥፋተኛውን ለመለየት በተደረገው መልኮታዊ ምርመራ የወደቀው መልአክ ዋና ተጠያዊ ሆኖ በመገኘቱ በሰይጣን ላይ፣ "በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ" (ዘፍ 3፡15) የሚል ትንቢት አዘል የእርግማን ቃል ተላልፏል። እዚህ ላይ "በዘርህ" የተባለ ሰይጣን የሚወልድና የሚራባ ሆኖ ሳይሆን የአዳምን ውድቀት ተከትሎ የሚገታውና የሚቋቋመው ኃይል ሳይኖር ትውልድን ሁሉ ሲተናኮል የሚኖር መሆኑን ሲያመለክት ነው። በሌላ በኩል ግን "በዘርዋ" የተባለው ይህን የጥፋት ኃይል የሚገታና የሚቋቋም ከሄዋን ዘር የሚወለደ መሆኑን ያመለክታል። የዚህ ትንቢት ፍጻሜ ሲደርስ ዳግማዊት ሄዋን ከተባለች ከድንግል ማርያም የተወለደችው ክርስቶስ የእባቡን ራስ በበትር (በከበረ መስቀሉ) ቀጥቅጦ ድልን አጎናጽፎናል። ዛሬም ይህን የክርስቶስ ደም የፈሰሰበት በትር  በእጃችን ይዘን በየዕለቱ ጠላታችንን እንከላከልበታለን። "የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና" 1ኛ ቆሮ. 118 ) ተብሎ እንደ ተጻፈ። ይህ በቀራንዮ አደባባይ ላይ የዲያብሎስ ራስ የተቀጠቀጠበት በደም የታጠበ በትር የክርስቶስ መስቀል ነው። ሙሴ ቀይ ባህርን የከፈለበትና ልዩ ልዩ ታምራትን ያደርገበት የእጁ በትር (ዘፍ 4፡17)፣ እንዲሁም "ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል፥ ከእስራኤል በትር ይነሣል" (ዘኁ 24፡17) ተብሎ ትንቢት የተነገረለት በትር የክርስቶስ መስቀል ነው። ቅዱስ ዳዊትም የክርስቶስ መስቀል ዋስትናችን መሆኑን ሲገልጽ፣ "በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኵዝህ እነርሱ ያጸናኑኛል" (መዝ 23፡4) ይላል።

 

 (ሠ) ሰውና እግዚአብሔርን አንድ ያደረገች የመገናኛ ድንኳ (የቃል ኪዳኑ ጽላት) በመሆኗ

     የእስራኤል ጠባቂ እግዚአብሔር ሰውን ከመውደዱ የተነሳ አስቀድሞ ለሙሴ የቃል ኪዳኑን ጻላት ሰጠ፤ በእርሷም አማካኝነት ከሕዝቡ ጋር እየተገናኘ የትድግና (የማዳን) ሥራውን አከናወነ (ዘፀ 25፡22፣ ዕብ 9፡4)። በዚሁ ምሳሌ እግዚአብሔር በእርሷ አድሮ እስራኤል ዘነፍስን ይታደግ ዘንድ ቅድስት ድንግል ማርያምን መረጠ። ስለዚህ ቅድስት ድንግል ማርያም የሐዲስ ኪዳን ሕግ የተጻፈበት የሕግ ጻላት፣ (ዘዳ 31:26፣ ዮሐ 1:14)፣ የሰው ልጆች የድኅነት ማዕከልና የምሕረት አደባባይ፣ መና የያዘች የወርቅ መሶበ፣ የድኅነት ቃል የተጻፈባት የወርቅ ሰሌዳ ናት። የቃል ኪዳኑ ጽላት በወርቅ የተለበጠች ነበረች። ቅድስት ድንግል ማርያምም ሁለተናዋ እንደ ወርቅ በንጽሕና ያጌጠ ነው። የቃል ኪዳኑ ጽላት በአቢዳራ ቤት ለሦስት ወራት በክብር ስለ ተቀመጠ እግዚአብሔር የአቢዳራን ቤት ባርኮለታል (2 ሳሙ 6:14)። በተመሳሳይ ሁኔታ ቅድስት ድንግል ማርያም በዘካርያስ ቤት ለሦስት ወራት በመቀመጧ ቤተሰቡ በረከትን አግኝቷል (ሉቃ 1:56)። በሌላ በኩል ደግሞ የቃል ኪዳኑ ጽላት ከእግዚአብሔር የተሰጠ ክቡር ስለሆነ ሳይገባው የሚነካ ይቀሰፍ ነበር (2 ሳሙ 6፡7)። ስለዚህም ቅዱስ ዳዊት ታቦተ ጽዮን ወደ ቤቱ በመጣች ጊዜ "የእግዚአብሔር ታቦት ወደ እኔ እንዴት ይመጣል?" (2 ሳሙ 6፡9) ሲል ለታቦተ እስራኤል ያለውን ክብር ገለጸ። በተመሳሳይ ሁኔታ ድንግል ማርያም ቅድስት ኤልሳቤጥን ልትጠይቃት በሄደች ጊዜ "የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?" (ሉቃ 1፡43) ብላለች። ቅዱስ ዳዊት ለታቦተ ጽዮን ያለውን ክብር በእስክታና በውዝዋዜ ገልጿል (2 ሳሙ 6፤14)። በተመሳሳይ ሁኔታ ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድስት ኤልሳቤጥን በጎበኘቻት ጊዜ በማኅጸኗ ያለው ዮሐንስ ለድንግል ማርያም ያለውን ክብር በንቅናቄ እንደገለጸ ተጽፏል (ሉቃ 1፡44)። ስለዚህ ድንግል ማርያምን ማክበር እግዚአብሔርን ማክበር እንደሆነ ተገንዝበን ከመሳሳት እንጠንቀቅ።

 

(ረ) የአማላጅነትና የአዳኝነት ወሰን በቅድስት ድንግል ማርያም

በ1054 ዓ.ም. በሮማን ካቶሊክና በምሥራቅ ኦሮቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ለተፈጠረው ትልቁ ክፍፍል (The Great Schism) እያሉ ለሚጠሩት መለያየት ምክንያት ከሆኑት የዶግማ ችግሮች አንዱ ካቶሊኮች ቅድስት ድንግል ማርያምን ከሚገባት በላይ አጋነው የአምላክነትን ጸጋ ማጎናጽፍ መጀመራቸው ነው። አሁን አሁን ስህተታቸውን ተረድተው ትምህታቸውን ለማስተካከል እየሞከሩ ቢሆንም በዚያ ዘመን ቅድስት ድንግል ማርያምን "ከሰማይ የወረደች ሉዓላዊት" ወይም "ኃይል አርያማዊት" እስከ ማለት ደርሰው እንደነበር አሁን ድረስ በእጅ ያሉ መረጃዎች ያመለክታሉ። በዚያ ዘመን ከተከሰቱትና አሁንም ድረስ በሮም ቤተ ክርስቲያን ከሚታመንባቸው የዶግማ ትምህርቶች አንዱ ድንግል ማርያምን "ተባባሪ አዳኝ Co-Redemptrix" ብሎ መቀበል አንዱ ነው።

        የኦሬንታል አብያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ በመላው ኦርቶዶክስ እንደሚታመነው አዳኝ ዓለምን በጥበቡ የፈጠረ፣ የፈጠርውንም ዓለም ሊታደግ በሥጋ የተገለጠ፣ በባሕርይው አምላክ የሆነ አንድ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። "እኔ፥ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከእኔ ሌላም የሚያድን የለም" (ኢሳ 43:11)። "ብቻውን ለሆነ አምላክና መድኃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ይሁን፤ አሜን" (ይሁዳ 1:25)።

  ቅድስት ድንግል ማርያም የድኅነት በር፣ "አንቀጸ-ብርሃን"- የብርሃን መገኛ፣ "ወሙዳየ ቅዱስ ቁርባን"- "መናውን ያስገኘችልን የወርቅ ሙዳይ" ብለን እንጠራታለን እንጅ እርሷ ራሷ አዳኝ፣ መድኃኒት ወይም እርሷ ራሷ የሕይወት መና ናት ብለን አናስተምርም። የአምላክ እናት በተሰጣት ቃል ኪዳን ታማልዳለች ብሎ ከመግለጽ ባለፈ የሚቀርብ የተጋነነ ትምህርት የዶግማ ትምህርታችንን አዳጋ ላይ ይጥላል። ጥንታዊያን የቤተ ክርስቲያን አባቶች ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ማላጅነት የተናገሩትን ከዚህ በታች እንመልከትና እነዚህ ጥቅሶች ድንግል ማርያምን በእግዚአብሔር ፋንታ አስቀምጠው አዳኝ ይሉ እንደሆነ ልብ ብለን እንመርምር።

 

የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት በቤተ ክርስቲያን አባቶች አንደበት፦

·    120 የተወለደ አይራንዮስ የተባለ የቤተ ክርስቲያን አባት፣ "በድንግል ማርያም የተማመነ ፈጽሞ አይጠፋም"።

·    በ306 የተወለደ ቅዱስ ኤፍሬም ዘሶርያ "ድንግል ሆይ እኛን በምህረት ዓይን መመልከትሽን አታቋርጭ፤ በርኅራኄሽ ክንፍ ስር አስጠልይን፤ ከእግዚአብሔር በታች ከአንች በቀር ሌላ የለንምና"።

·    በ347 የተወለደ ቅዱስ ጀሮም የተባለ የቤተ ክርስቲያን አባት፣ "ቅድስት ድንግል ማርያም ስሟን ስንጠራት የምትመጣ ብቻ ሳይሆን ፈጥና ከተፍ የምትል ናት"።

·   በ330 የተወለደ የቂሳራያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ባስልዮስ፣ "እግዚአብሔር በሁሉም መንገድ ትረዳን ዘንድ ሹሟታል"።

·    በ460 የተወለደ ቅዱስ ፈልጊንቱስ የተባለ ሊቀ ጳጳስ "ድንግል ማርያም የመንግሥተ ሰማያት መሰላል ናት፤ በእርሷ አምላክ ከሰማያት ወርዷልና እንዲሁም ሰዎች በእርሷ አማካኝነት ከምድር ወደ ሰማይ ይወጣሉ"። 

·    በ676 የተወለደ የደማስቆ ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ዮሐንስ "የአምላክ ናት ሆይ በአንች ብተማመን እንደምድን አምናለሁ፤ በአንች ጥበቃ ስር ከሆንኩ የምፈራው ነገር የለም፤ በአንች ጥላ ስር መሆን ማለት ድኅነትን ማግኘት ማለት ነውና"።    

   እናማ ኦርቶዶክሳዊያን የቅድስት ድንግል ማርያምን ክብር ሲገልጹ የሚሰጣት ክብር መጠኑን እንዳያልፍና "Co-Redemptrix" (ተባባሪ አዳኝ) ከሚለው የካቶሊክ ትምህርት ጋር እንዳይዛመድ ልዩ ጥንቃቄ ያደርጋሉ።

   ይሁን እንጅ አሁን አሁን ፕሮቴስታንቶች በቅድስት ድንግል ማርያም ላይ የሚያስተምሩትን የነቀፋ ትምህርት ለመቃወምና በተቃራኒውም ጸረ-ማርያም ላለመባል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያለ አንዳች ሳምሱር (ቀኖናዊ ፍተሻ) በየሙዚቃ ቤቱ በግለሰቦች የሚደረሱ መዝሙሮችም ሆኑ ያለ አንዳች ቁጥጥር በየመድረኩ ስለ ድንግል ማርያም እየተሰጡ ያሉ ትምህርቶች በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይሰጣሉ ብሎ ለማመን ይከብዳል። ትውልዱ ቅድስት ድንግል ማርያምን የወደደና ያከበረ እየመሰለው ሁላችንም ሳናውቀው ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብተን እንዳንገኝ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል። (ወደፊት በዚህ ርዕስ ላይ ሰፋ ያለ ሐተታ ለማቅረብ ዝግጁ መሆኔን ከወዲሁ ልግልጽ እወዳለሁ)።

 

(ሰ) የእረፍቷና የዕርገቷ ታሪክ በትውፊትና በሃይማኖት አባቶች አንደበት

  ቅድስት ድንግል ማርያም በአካለ ሥጋ እያለች በቅድስናዋ፣ በንጽሕናዋ፣ በጭምትነቷና ወሰን በሌለው ትኅትናዋ ምሳሌ የሆነችን ያህል እንቀላቀላት ዘንድ ተስፋ ለምናደርጋት በሰማያዊት ቤተ ክርስቲያን ለዘለዓለሙ በደስታ ለመኖር የመጀመሪያዋ ሰው ነች። ቅድስት ድንግል ማርያም በእውነት አርጋ ቢሆን ኖሮ ቅዱሳን ሐዋርያት በወንጌል ውስጥ ይዘግቡት ነበር በሚል የሚከራከሩ አይጠፉም። ታሪኳ በትክክል በወንጌል መጻፍ ካለበት ዕርገቷ ብቻ ሳይሆን መላ ሕይወቷ ይልቁንም አስገራሚው እረፍቷ መገለጽ ነበረበት። ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ያልተገለጸውን ሁሉ አንቀበልም የሚሉ ከሆነ ስለ ሞቷ ምንም ዓይነት መረጃ ማግኘት አይችሉም።    

·    ከ422 to 458 የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ የነበረው ቅዱስ ጁቬናል፦

    "ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱሳን ሐዋርያት በአሉት ከሥጋ ድካም አርፋለች። ሆኖም በሐውርያው ቶማስ ጠያቂነት መቃብሯን በከፈቱ ጊዜ ሥጋዋን አላገኙትም። በዚህም ምክንያት ቅዱሳን ሐዋርያት በሥጋ አርጋለት ከሚል ድምዳሜ ደረሱ"።

·  በ354 ዓ.ም. የተወልደው ኦገስቲን የተባለ የላቲን ክርስቲያኖች አባት እንዲህ ብሏል፣ "ይህ የከበረ በዓል ቀን ነጋ፤ ይህም ከቅዱሳን የክብር በዓላት ሁሉ የከብረና ከፍ ያለ የድንግል ማርያም በዓል የአምላክ እናት ከዓለም ድካም አርፋ ሥጋዋ መበስበስን ሳያይ ወደ ሰምያዊ ያረገበት ቀን ነው። በዚህ ቀን ልዕልት ድንግል ማርያም በቅዱሳን አድናቆትና ምስጋና ወደ አብ የክብር ዙፋን ተወሰደች፤ ከበረች፤ ከፍ ከፍም አለች"።

·   538 – 594 የሮም ሊቀ ጳጳስና የታሪክ ጽሐፊ የነበረው ቅዱስ ጎርጎሪዮስ ዘቶርስ በቅድስት ድንግል ማርያም ዕረፍት ወቅት ጌታ በቅዱሳን መላእክት ታጅቦ እንደመጣና በመላእክትና በቅዱሳን ዝማሬ ታጅባ ነፍሷ ከሥጋዋ በክብር እንደተለየ ከገለጸ በኋላ በመቀጠል እንዲህ ይላል፣ "እነሆ ለሁለተኛ ጊዜ ጌታ በመካከላቸው ቆመ፤ ቅዱስ ስጋዋም በገነት እንዲያርፍ አዘዘ፤ የድንግል ማርያም ሥጋ ከተመረጡት ቅድሳን ጋር ከበረ፤ ፍጻሜ የሌለው የዘለዓለማዊነት ክብርንም ተቀዳጀ"።

·  ከ550- 650 የነበረ ቴዎቴክኖስ ዘሊቪያስ የተባለ ሊቀ ጳጳስት፦

    "የመለኮት እናት አምላክን የተሸከመች የቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ሥጋ በመለኮታዊ ጸጋ ያሸበረቀ እድፈት የሌለበት ንጹሕ እንደመሆኑ እንደ ሰው ለጊዜ አፈርን ይለብስ ዘንድ ግድ ቢሆንም ወደ ሰምያት ያርግና ለዘለዓለሙ በክብር ከፈጣሪ ጋር በደስታ ይኖር ዘንድ የሚገባ ነው"።

·   በ630 ሞደስተስ የተባለ በኢየሩሳሌም የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ የነበረ፦

    "የሕይወታችን አስገኝና ዘለዓለማዊነትን የሚሰጥ መድኃኔዓለም ክርስቶስን የወለደች ፍጹም ባለክብር የአምላክ እናት ሕይወትን ከእርሱ እንደተቀበለች ሁሉ በሥጋ ከመፍረስና ከመበስበስ ነጻ ሆኖ ለዘለዓለም መኖርንም በእርዙ ዘንድ አግኝታለች። ስለዚህም ከመቃብር አንስቶ እርሱ ባወቀ ቦታ ከእሩሱ ጋራ ለዘለዓለም ያኖራት ዘንድ በክርብ ወደ ላይ አርጋለች"።

·   ከአምስቱ የኦሬንታል አብያተ ክርስቲያናት አንዷ የሆነችው የጥንታዊት አርሜንያን ኦርቶዶክስ የቅዳሴ መጽሐፍ፦

  "በዛሬው ዕለት ቅዱሳን መላክእክት የመንፈስ ቅዱስ መኖሪያ ወደ ሚሆን ወደ ሰማይ የቅድስት ድንግል ማርያምን ሰውነት ይዘው መጡ፤ በኢየሩሳሌም ሰምያዊት በንጹሕ ድንኳን በሥላሴ አጠገብ በክብር እንድታርፍ አደረጉ"።

  "ዛሬ የሰማይ መላእክት የወላዲተ አማልክን አካል ወደ ሰምይ ይዘው ወጡ፤ በመላእክት መካከልም አሳረፉት፤    በቃላት ሊገለጽ የማይችል ደስታን ታገኝ ዘንድ"።

  "በዚህ ሰውነት ዘመንሽን ሁሉ በንጽሕና በቅድስና ኑረሽ እነሆ ዛሬ በጌታ መለኮታዊ ፈቃድ አማላካችን ወደ ሚሆን ወደ ልጅሽ መንግሥት በክብር ገባሽ፤ ድንግል ሆይ ለምኝልን"።

 

የቅድስት ድንግል ማርያም ጸጋና በረከት አይለየን፤ አሜን

ቀሲስ ዘመነ ደስታ