ወላዲተ አምላክ በኦርቶዶክስ ትውፊት

ክፍል ሁለት

መግቢያ፦ ቅድስት ድንግል ማርያም በክርስትና ሃይማኖት ያላትን ትክክለኛ ቦታ ለይቶ ማወቅ የትክክለኛ እምነት ማረጋገጫ ነው። ቅድስት ድንግል ማርያም እንደሚገባ የተገለጸችበትና በቤተ ክርስቲያን ለክብሯ የሚገባውን ተመጣጣኝ ወዳሴ ያገኘችበት የእምነት ተቋም ካለ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ነው። የድንግል ማርያም ትምህርት (Mariology) በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በጣም የተጋነነ ሲሆን በፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ በእጅጉ የወረደ ነው።

          ሉተራዊያን የቤተ ክርስቲያንን ቀጥተኛ አስተምሕሮ ተውቃውመው (ፕሮቴስት አድርገው) ከጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ሲወጡ የተቃውሞ ቀስታቸው አስቀድሞ ካነጣጠረባቸው ነባራዊ እውነታቸው አንዱ የቅድስት ድንግል ማርያምን ክብር መጋፋት ነው። ሆኖም በሰዎች አድሮ የተቃወማት ዓለም በልጇ ደም በመዳኑ የተቆጨ ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ስለ ድንግል ማርያም ስደትና ስለ ቀጣዩ የክርስትና ፈተና በጻፈበት በራዕይ 12 የአምላክ እናት ክርስቶስን አዝላ ለ3 ዓመታት ተኩል ያህል መሰደዷን በምሳሌያዊ አነጋገር (Typology) በዝርዝር ከገለጸ በኋላ አውሬው ይህ የጥፋት ሕልሙ ባለመሳካቱ እርሷንና ተከታዮቿን ሊያጠቃ እያደረሰ ያለውን ጥፋት እንዲህ ሲል በተጨማሪ ያብራራል። "እባቡም ሴቲቱ በወንዝ እንድትወሰድ ሊያደርግ ወንዝ የሚያህልን ውኃ ከአፉ በስተ ኋላዋ አፈሰሰ። ምድሪቱም ሴቲቱን ረዳቻት፥ ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን ወንዝ ዋጠችው ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቈጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ፤ በባሕርም አሸዋ ላይ ቆመ" (ራዕይ 12፡13-16)።

          አውሬው በስተኋላዋ ያፈሰሰው ማዕበል የተቀላቀለበት ውሃ የጥላቻና የሁከት መንፈስ ነው። ውሃ ለበረከት ሲሆን የረከሰውን ይቀድሳል። ለቁጣ ሲላክ ደግሞ ዓለምን ይደመስሳል። "የጥፋትም ውኃ በምድር ላይ አርባ ቀን ነበረ" (ዘፍ. 7፡17) ተብሎ እንደተሳፈ። አውሬው ዛሬም ስመ አጠራሯን ለማጥፋት ሐዋርያው እንደጠቀሰው ከዘርዋ የቀሩትን ማለትም በአማላጅነቷ የሚተማመኑትንና ለክብሯ የቆሙትን ለአማሳደድ ተግቶ ይሠራል። በአንድ በኩል ክብሯን ለሚነቅፉ ሰዎች የቃላት ሾተልን ያቀብላል። በሌላም በኩል ወደፊት በክፍል ሦስት እንደምንመለከተው በእናታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ላይ ያነጣጠረውን ፕሮቴስታንታዊ ጥላቻ ለመቃወምና የአማላጅነት ጸጋዋን ለመከላከል በሚል የኦርቶዶክስ ልጆች የአምላክነት ክብርን እንድናጎናጽፋት በማድረግ ክፉ መንፈስ ከመስመር እንድንወጣ ተጨማሪ የስህተት መንገዶችን እያመቻቸልን ይገኛል። ሆኖም በቅድስት ድንግል ማርያም ዙሪያ የሚነገሩ የክህደትና የጥርጣሬ ትምህርቶች ሁሉ በሊቃውንት ትምህርት መክነው እንደሚቀሩ ሲግልጽ ሐዋርያው "ምድሪቱም ሴቲቱን ረዳቻት…አፍዋን ከፍታ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን ወንዝ ዋጠችው" ይላል። ምድር የተባሉ በምድር የሚኖሩ ወንጌላውያን መሆናቸውን "ሰማይ ትስማ ምድርም ታድምጥ" (ሚክ 1፡2) ከሚለው የነቢዩ ቃል መረዳት ይቻላል።   

 

የቅድስት ድንግል ማርያም ክብር በዓለም ድኅነት ላይ ካላት ቦታ አንጻር

The Veneration of the Theotokos and Her Role in the Christian Economy of Salvation

የዶግማ ተፋልሶ የሚያስከትሉ በቅድስት ድንግል ማርያም ላይ ያነጣጠሩ መሠረታቸውን የለቀቁ ትምህርቶች መነሻቸው አንድም ቅድስት ድንግል ማርያም የአማላክ እናት ከመሆኗ አንጻር በዓለም ድኅነት ላይ ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ካለመረዳት ወይም ወላዲተ አምላክ መሆኗን በማጋነን ሰው መሆኗን ከመዘንጋት የሚመጡ ናቸው። በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ወላዲተ አማላክ ማርያም ከፍጡራን ሁሉ በላይ የከበረች መሆኗ የተመሰከረ ቢሆንም ይህ ልዕልናዋ አምላክን ከመውለዷና ለዓለም ድኅነት ካበረከተችው አስተዋጽኦ ጋር የተገናዘበ መሆኑን ልብ ብሎ ማስተዋል ያስፈልጋል። ስለዚህም ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ ሲጽፍ "ወላዲተ አምላክ ማርያም የአምላክ እናት መሆኗን የሚጠራጠር ሁሉ ከእግዚአብሔር የተለይ ይሁን" ይላል። እንዲሁም የግብፁ ፓትርያርክ አባ ሽኖዳ "ቅድስት ድንግል ማርያምን የሚያከብር ሁሉ በዚህ እምነቱ ክርስቶስን እንዳከበረ ሊረጋገጥ ይገባዋል" ይላሉ። ቅድስት ድንግል ማያርያምን የምናከብርበት ዋና ዋና ምክንያቶች፦

 

(ሀ) "በአማን ወላዲተ-አምላክ" /በእውነት የአማላክ ናት/ (Theotokos - Bearer of God) በመሆኗ፣

በክርስትና ስም የሚጠሩና ሰው የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን በአምላክነቱ የሚቀበሉ አብያተ ክርስቲያናት ቅድስት ድንግል ማርያምን "ወላዲተ-አማላክ" ብለው ለመቀበል አይቸገሩም። መለኮት "ከሥጋዋ ሥጋን እንጅ ነፍስን አልነሳም" ወይም ዳዊት በማኅደር ውስጥ እንደሚቀመጥ "ገብቶ ወጣ" (አደረባት) እንጅ "ስጋንም ደምንም አልተዋሐደም" የሚሉ ከሆነ ግን ድንግል ማርያምን "ወላዲተ-አምላክ" ብሎ ለመቀበል ይቸገራሉ። ምክንያቱም በዚህ የኅድረት ትምህርት መሠረት ድንግል ማርያምን የተራ ሰው እናት እንጅ የአምላክ እናት ለማለት ያስቸግራልና። በ431 ዓ.ም. በሦስተኛው ዓለም አቀፍ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ በኤፌሶን የተወገዘው መናፍቅ ንስጥሮስ ያስተማረው ትምህርት ይህ ነበር። ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ-ሰብዕ ወይም ወላዲተ-ክርስቶስ እንጅ ወላዲተ-አምላክ አትባልም በማለቱ በቅዱስ ቄርሎስ የተዋሕዶ ትምህርት ተረትቶ በውግዘት ከቤተ ክርስቲያን አንድነት ተልይቷል። የንስጥሮስ ቤተ ክርስቲያን (Asyrian Church -Church of the East) ለብዙ መቶ ዓመታት ይህንኑ በአባቶች የተወገዘ እምነት ስታራምድ ቆይታ ቀስ በቀስ በአማኞች መካከል በተፈጠረው መከፋፈል ምክንያት እየከሰመች ብትመጣም "አደረባት እንጅ ከነፍሷ ነፍስን ከሥጋዋ ሥጋን አልነሳም" የሚለው ያረጀ አመለካከት ዛሬም የፕሮቴስታንቶች እምነት ሆኖ ቀጥሏል።

          በኦርቶዶክስ ትምህርት ክርስቶስ "ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው" ነው። ይህንም ለመረዳት የሰው ልጅን ሥነ-ተፈጥሮ ልብ ብሎ ማጤን ያስፈልጋል። የሰው ዘር በእግዚአብሔር ልዩ አፈጣጠር ሕያዊት ነፍስን ካገኘ በኋላ (ዘፍ 2፡7) "ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት" (ዘፍ 9፡1) በተባለው አምላካዊ ቃል ኪዳን መሠረት በጽንስ ወቅት ከአናቱና ከአባቱ አካልን ብቻ ሳይሆን ነፍስን ጭምር እየተካፈለ ይራባል እንጅ እግዚአብሔር በየዕለቱ ሲፈጥር ይኖራል ወይም በእያንዳንዱ አዲስ አካል ውስጥ ነፍስን ያሳድራል ተብሎ አይታመንም። በሌላ በኩል ደግሞ የዓለም ድኅነት በክርስቶስ መታወጁን የምናምን ከሆነ መለኮትና ሥጋ በፍጹም ተዋሕዶ አንድ ካልሆኑ ወይም ክርስቶስ የእኛን ሥጋ ነስቶ ፍጹም ሰው ካልሆነ አምላክ እኛን ለማዳን ሲል ሞተ ብሎ መናገር እንደማይቻል መገንዘብ ያስፈልጋል። ስለ እርቅ የፈሰሰው በየዕለቱ የምንቀበለው ሥጋና ደም ድኅነትን ያስገኛል ብሎ መናገር አያስደፍርም። "ሞተ በሥጋ ወኃይወ በመንፈስ" - “በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ” (1ጴጥ.3፡18) ሲል ቅዱስ ጴጥሮስ የተናገረው ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው መሆኑን በማረጋገጥ ነው። ቅዱስ ጳውሎስም "በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ" (የሐዋ 20፡28) በማለት ስለ እኛ ሲል በቀራንዮ አደባባይ የተሰቀለው ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ መሆኑንና ከድንግል ማርያም በነሳው ሥጋ ፍጹም ሰው መሆኑን ይመሰክራል።

          ሊቁ ቅዱስ ቄርሎስ የክርስቶስን አምላክነትና ሰውነት በተናገረበት ድርሳኑ እንዲህ ይላል፣ ወልድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማይመረመር ተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነውና ቀዳማዊ ሲሆን ከዘመናት አስቀድሞ ከአብ የተወለደ ነው...ዳግመኛ በሥጋ እንደተወለደ ስለእርሱ እንዲህ ይነገራል እንደሰው ሁሉ አስቀድሞ ቅርጽ የተፈጸመለት ሰው ተገኝቶ ከዚህ በኋላ ቃል ያደረበት አይደለም በእመቤታችን ማሕጸን እርሱ ብቻ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነ እንጅ በሥጋም ይወለድ ዘንድ ወደደ በሥጋ መወለድንም ለእርሱ ብቻ ገንዘብ አደረገ (ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ 73 4-5)

          ከ35 ዓመተ ምህረት አስቀድሞ እንደተወልደ የሚነገርለትና ስለ ክርስቶስ ጽኑ መከራን በመቀበሉ የሚታወቀው ታላቁ ሰማዕት የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ አግናጥዮስ አምላክ በተዋሕዶ ፍጹም ሰው መሆኑን በማይቀበሉ ሰዎች ትምህርት ልቡ ተነክቶ በሀዘን ቃል እንዲህ ያላል፣ "ከእግዚአብሔር በአፍኣ የሆኑ የማያምኑ ሰዎች እንደተናገሩ እግዚአብሔር ሰው የሆነው በታይታ በምትሐት ከሆነ፣ በእውነት ሥጋን ካልነሳ፣ የሞተው መከራን የተቀበለው በምትሐት እንጂ በእውነት ካልሆነ፤ እኔ በምን ምክንያት ስለእርሱ እታሰራለሁ፣ ራሴንስ ለተራቡ አናብስት ለመስጠት ስለምን እቸኩላለሁ? እንዲህ ከሆነ ሞቴ ከንቱ ነዋ! ክርስቶስን በመከራው ለመምሰል መከራን የምቀበል እኔ ሐሰተኛ ነኛእንዲህም ከሆነእነርሱም ወደ ወጉት ይመለከታሉ ሰውም ለአንድያ ልጁ እንደሚያለቅስ ያለቅሱለታል፥ ሰውም ለበኵር ልጁ እንደሚያዝን በመራራ ኀዘን ያዝኑለታል ያለ ነቢዩ ከንቱ ተናገራ! (ዘካ.12:10) እነዚህ ሰዎች ከሰቃልያን አይሁድ የማይተናነሱ የማያምኑ ናቸው እኔስ አለኝታየን በማስመሰል፣ በምትሐት በሞተልኝ ላይ አላደርግም፤ በእውነት ነው እንጂ ድንግል ማርያምም በእውነት እግዚአብሔር የተዋሐደውን ሥጋ በማኅፀኗ ተሸከመች እግዚአብሔር ቃልም እንደእኛ ሕማም ሞት የሚስማማው ሥጋን ተጋርዶ በእውነት ከድንግል ተወለደ ሰውን ሁሉ በማኅፀን የሚስል እርሱ በእውነት በማኅፀን ኖረ፤ ከድንግልም ያለ ሩካቤ ለራሱ ሥጋን አዘጋጀ እንደእኛ ዘጠኝ ወር በማኅፀን አደረ፣ እንደእኛ በእውነት ተወለደ፣ እንደእኛ በእውነት ጡትን ጠባ፣ በላ ጠጣ 30 ዘመናት ከሰው ጋር ከተመለሰ በኋላ በዮሐንስ እጅ በምትሐት ሳይሆን በእውነት ተጠመቀ ሦስት ዓመት ወንጌልን አስተማረ ታምራት አደረገ ፈራጅ ሲሆን በአይሁድ በሐሰት ተፈረደበት፣ በገዥው በጲላጦስ ተገረፈ፣ በጥፊ ተመታ፣ በማስመሰል በማታለል ሳይሆን በእውነት ተሰቀለ በእውነት ሞተ፣ ተቀበረ፣ ከሙታንም ተለይቶ ተነሣ"  (ለትራልያንስ የተላከ መልእክት ምዕራፍ 10)።

 

የወላዲተ አምላክ ክብር በትውፊትና በመንፈስ ቅዱስ ምስክርነት ሲረጋገጥ

ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ስናስብ ታሪኳ በመጽሐፍ ቅዱስ ተዘርዝሮ ባይጻፍም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በትንቢት፣ በምሳሌና በትውፊት ስለ እርሷ ሲነገር የኖረ ከቁጥር በላይ የሆነ ማስረጃ እናገኛለን። ለምሳሌ ቅድስት ድንግል ማርያም የመጥምቀ መለኮት ዮሐንስን እናት ልትጎበኛት በሄደች ጊዜ ቅድስት ኤልሳቤጥ "የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?" (ሉቃ 1፤42) በማለት የተናገረችውን ቃል እናስብ። ድንግል ማርያም የአምላክ እናት መሆኗን ወይም በቅድስት ድንግል ማርያም ማኅጸን ያደረው (የተጸነሰው) ሰምይና ምድርን የፈጠረ አምላክ መሆኑን ለቅድስት ኤልሳቤጥ ማን ነገራት? ይህን ጥያቄ ለመመለስ ሁለት ነገሮችን ማስተዋል ይገባል።

              በአንድ በኩል አምላክ ሰውን ለማደን በሥጋ እንደሚገለጥ ለዚህም አማላካዊ ተልዕኮ መሳካት እርሱ ራሱ ያዘጋጃት ከአዋልደ እስራኤል መካከል ለራሱ ማደሪያነት የመረጣት ሴት በጊዜው እንደምትገለጥ ቃል በቃል የተላለፈ በመጽሐፍም የተገለጠ ትንቢት በመኖሩ ነው። "እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች" (ኢሳ 7፡14) የሚለውን ትንቢት ማሰብ ይገባል። እዚህ ላይ በትውፊት ሲነገር የኖረ ትንቢት በጊዜው እውን ሆኖ መገለጡን እናያለን።

          ሁለተኛው ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ምስክርነት ነው። ቅድስት ኤልሳቤጥ ይህን ሊታመን የማይችል ምስክርነት የሰጠችው በግምት ሳይሆን አምላክ በራሱ የጊዜ ቀጠሮ ሰው መሆኑን እንድትረዳ መንፈስ ቅዱስ ስለ ገለጸላት ነው። "በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት" የሚለው ቃለ ለዚህ አባባላችን እውነተኛ ማረጋገጫ ነው። እግዚአብሔር ለቅድስት ኤልሳቤጥ ምን ምን ምሥጢሮችን ነገራት የሚለውን እንደገና ማሰብ ይገባል። አራት ነገሮችን አስረግጦ ነገሯታል። 

(1) በድንግል ማርያም ማኅጸን ያደረው (የተጸነሰው) ከኃጢአት ቁራኝነት ይታደገን ዘንድ በፈቃዱ ሰው    የሆነ አምላክ ወልደ አማላክ መሆኑን ("የጌታየ እናት" ቁጥር 43)፤

(2) ቅድስት ድንግል ማርያም ከሴቶች ሁሉ የተለየችና የከበረች፣ መርገመ ሥጋ መረገመ ነፍስ የሌለባት፣   በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን የምታሰጥ አማላጅ መሆኗን ("ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ" ቁጥር 42)፤

(3) በቅድስት ድንግል ማርያም ማኅጸን ያደረው ጌታ በባሕርይው ስግደትና ምስጋና የሚገባው አምላክ   ወልደ አምላክ መሆኑን ("የሰላምታሽ ድምጽ በጆሮዬ በመጣ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና"  ቁጥር 44)፤

(4) ጽንሰቷ በብሥራተ መልአክ የተፈጸመ መሆኑንና ቅድስት ድንግል ማርያም የመልአኩን ቃል "አሜን" ብላ በመቀበሏ የተመሰገነች መሆኗን "ከጌታ፤ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት" (ቁጥር 45)። እርሷ ራሱም ይህን የምስጋና ቃል በማሰብ "ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል" (ቁጥር 48) ብላለች። ይህም አስቀድሞ "ለእናትዋ አንዲት ናት…ቈነጃጅትም አይተው አሞገሱአት፥ ንግሥታትና ቍባቶችም አመሰገኑአት። ይህች እንደ ማለዳ ብርሃን የምትጐበኝ፥ እንደ ጨረቃ የተዋበች እንደ ፀሐይም የጠራች፥ ዓላማ ይዞ እንደ ተሰለፈ ሠራዊት የምታስፈራ ማን ናት?" (መኃ 6፡9) ተብሎ ትንቢት የተነገረላት እርሷ መሆኗን ያመለክታል።

በአጠቃላይ የዮሐንስ እናት ኤልሳቤጥ ለድንግል ማርያምና በማኅጸኗ ላደረው ጌታ በተመሳሳይ ሁኔታ (የተባረከ) (የተባረክሽ) የሚሉ ቃላትን መናገሯና በተለይም ደግሞ ለቅድስት ድንግል ማርያም "ብፅዕት" ብላ ታላቅነቷን መመስከሯ ቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክ እናት በመሆኗ ክብር፣ መሥጋናና ውዳሴ የሚገባት መሆኑን ያረጋግጣል።

 

(ለ) የኃጢአት ደዌ ላደቀቀው ትውልድ መድኃኒትን ያስገኘች ባለውለታ መሆኗ፣

  በሽታችን ጸንቶብን ወደ ሆስፒታል ከሄድን በኋላ ለበሽታችን ተስማሚ የሚሆን መድኃኒት ታዞልን ስንፈወስ  በተለምዶ "ዶክተሩ አዳነኝ" እንላለን። ያደነን መድኃኒቱ እንጅ ዶክተሩ እንዳልሆነ ቢታወቅም በሽታችንን ለማግኘት ተጨንቆ ስለ ረዳንና ከመድኃኒቱ ጋር ስለ አገናኘን ባለውለታችን ነው። የግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ለኃጢአተኞች ፍውስ ይሆን ዘንድ በሥጋ የተገለጽ በመሆኑ "ባለ መድኃኒት" (ማር 2፡17) ተብሏል። ከመድኃኒት ጋራ የሚያገናኘን ሳይሆን እርሱ ራሱ በአማን የነፍሳችን መድኃኒት ነው፤ ስሙም "መድኃኔዓለም" ይባላል (ሉቃ 2፡11)። ቅድስት ድንግል ማርያምም በተመሳሳይ ሁኔታ መድኃኒትን ያስገኘችልን ባለውለታችን ናት። የአምላክ እናት በዓለም ድኅነት ላይ ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ስናዘክር የሚከተሉትን ታሳቢ በማድረግ ነው። 

 

(1)  የአምላክ እናት እንድትሆን መመረጧን በፈቃደኝነት በመቀበሏ

   አምላክ ከድንግል ማርያም ሰው የሆነው ነጻ ፈቃዷን ጠብቆ በብሥራተ መልአከ የይሁንታን ቃል ከአንደበቷ አግኝቶ ነው እንጅ በማስገደድ ወይም ሳታውቀው በምትሐት መልክ በውስጧ በማደር አልነበረም። እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም አምላክ ሰውን ለማዳን በሥጋ እንደሚገለጽ በትውፊት ሲነገር የኖረውን ቃል ስለ ምትረዳ ለጊዜው ይህ ጥሪ ግርማው በሚያስፈራ መልአክ በኩል ለእርሷ በመድረሱ ብትደናገጥም ራሷን ጨምሮ የሰው መዳን ፍላጎቷ በመሆኑ "ትጸንሲ" - "ትጸንሻለሽ" ለሚለው የመልአኩ የብሥራት ቃል "ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ" - "እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ" (ሉቃ1:38) በማለት በፈቃደኝነት ተቀብላለች። "መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች" (ሉቃ 1፡47) ያላችውም ለዚህ ነው። ስለዚህ አይቻለኝም የማለት ነጻነቷ የተጠበቀ ሆኖ ሳለ በፈቃዷ የመልአኩን ቃል ስለ ተቀበለች ለሰው ልጆች ድኅነት ከአምላክ ፈቃድ ጋር የተባበረች (1ቆሮ 3፡9) በተዋሕዶ ላይ ንቁ ተሳትፎ ያደረገች ባለውለታችን ናት።

               ስለዚህም ቅድስት ድንግል ማርያምን ሊቃውንት ጥፋትን በምሕረት የለወጣችና እናቷ ሄዋንን የካሰች የሴቶች ሁሉ ጠበቃ ነች ብለዋታል። ሄዋን ጀሮዋን ለሰይጣን ሰጠች፣ ለሰው ልጆች ውድቀትም ከሰይጣን ጋር ተባበረች፣ ትውልድን ወደ ሞት ገፋች። ቅድስት ድንግል ማርያም ግን የመልአኩን ቃል ሰማች፣ ለሰው ልጆች ድኅነት ከአማላክ ፈቃድ ጋር ተባበረች፣ መድኃኒትን አስገኘች፣ የሕይወት መሠረትም ሆነች።  

 

   (2) ሰውነቷን በንጽሕና በቅድስና ጠብቃ ራሷን በማዘጋጀቷ

ቅድስት ድንግል ማርያም የአዳም ዘር በመሆኗ እንደማንኛችንም ሥጋዊ ፈተና ሊያጋጥማት የሚችል ሆኖ ሳለ ንጽሕዋንና ድንግልናዋን ጠብቃ በመኖር ያበረከተችው አስተዋጽኦ ግምት ውስጥ ሳይገባ የሚታለፍ አይደለም። የድንግል ማርያምን ንጽሕና ልዩ የሚያደርገው ከተግባር ብቻ ሳይሆን ከሐልዮ ጭምር ንጹሕ መሆኗ ነው። "ወንድ ስለ ማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል?" (ሉቃ 1፡34) የሚለው አነጋገሯ ከእድፈት ንጽሕት መሆኗን ብቻ ሳይሆን በአእምሮዋ ውስጥ ከወንድ ጋር የመኖር ውሳኔ እንደሌላት ያረጋግጣል። በእርግጥ እዚህ ላይ በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ወላዲተ አምላክ በቅድስና ተጠብቃ የኖረችው ጌታ ራሱ ከእድፈት ጉድፈት ስለ ከለከላት ነው የሚልና ከ"አምላክ ቅድመ-ውሳኔ" (Predestination) ጋራ የሚገናኝ አመለካከት ቢኖርም አምላክ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው የሆነው ፈቃዷን በመጋፋት እንዳልሆነ አውቀንና ተረድተን ከዚህ አንጻር እርሷም በበኩሏ ራሷን በመጠበቅ በኩል በነጻ ፈቃዷ ያበረከተችው አስተዋጽኦ መኖሩን አስተውሎ መረዳት ያስፈልጋል።

     ሰሎሞን በትንቢቱ "ወዳጄ ሆይ፥ ሁለንተናሽ ውብ ነው፥ ነውርም የለብሽም" (መኃ 4፡7) ያላት ለዚህ ነው። ቅዱስ ዳዊት አስቀድሞ በትንቢቱ "ልጄ ሆይ፥ ስሚ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ፤ ወገንሽን ያባትሽንም ቤት እርሺ፤ ንጉሥ ውበትሽን ወድዶአልና፥ እርሱ ጌታሽ ነውና" (መዝ 45፡11) ያላት አምላክ በርድኤት ጥላ ስር ስለከለላት ብቻ ሳይሆን ራሷን በቅድስና ስለ ጠበቀችም ጭምር ነው። የእርሷ አስተዋጽኦ ሳይኖርበት ነጻ ፈቃዷ ተገድቦ እርሱ ራሱ ከእድፈት የከለከላት ከሆነ በንጽሕናዋ በቅድስናዋ ምክንያት መረጣት ለማለት ያስቸግራል። ስለዚህም ነው አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው "ወሶበ ርዕየ ንጽሕናኪ ለሊሁ እግዚአብሔር አብ ፈነወ ሐቤኪ መልአኮ ብርሃናዌ ዘስሙ ገብርኤል ወይቤለኪ መንፈስ ቅዱስ ይመጽእ ላዕሌኪ ወኃይለ ልዑል ይጼልለኪ" - "እርሱ እግዚአብሔር አብ ንጽሕናሽን ባየ ጊዜ ስሙ ገብርኤል የሚባል ብርሃናዊ መልአኩን ወደ አንች ላከ፤ መንፈስ ቅዱስ በላይሽ ይመጣል፣ የልዑል ኃይልም ይጋርድሻል አለሽ" ሲል የተናገረው (ቅዳሴ ማርያም ይመልከቱ)። በአጠቃላይ ቅድስት ድንግል ማርያም አምላክን ለመቀበል ራሷን የተሟላ ቤተ መቅደስ አድርጋ አዘጋጅታለች። እርሷን ከሌላው ሰው ልዩ የሚያድርጉ የቅድስና መስፈርቶች አሉ። እነሱም፣ ድንግልና፣ እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር፣ የራስን ፈቃድ ለአምላክ ፈቃድ ማስገዛት (ትህትና)፣ ታዛዥነት፣ ከፈጣሪ ጋር እየኖሩ መሆኑን ተገንዝቦ በየዕለቱ የሚድረግ ያልተቋረጠ ጸሎትና እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ ጠባቂነት መታመን (ጥበብ) ናቸው።

  

የቅድስት ድንግል ማርያም ጸጋና በረከት አይለየን፤ አሜን

ቀሲስ ዘመነ ደስታ

 

ይቀጥላል።