ክርስትና ያለ ትውፊት (Christianity without Tradition)

ክፍል አንድ

ክርስትና ያለ ትውፊት በሸክላ ስባሪ ላይ የበቀለ ተክል ማለት ነው። ሥር መሠረት የለውምና ፍሬ ሊያፈራ አይችልም። ቁጭ ብለህ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ በጀሮህ የምትሰማውና ለልጆችህ የምታስተላልፈው ታሪካዊ ውርስ በጽሑፍ ከምትቅበለው በእጅጉ ይበልጣል። ጻድቁ ኢዮብ እንዳለ "ዘመናችን በምድር ላይ እንደ ጥላ ነውና እኛ የትናንት ብቻ ነን፤ ምንም አናውቅም፤ ስለዚህ የቀደመውን ትውልድ ጠይቅ፥ አባቶቻቸውም ለመረመሩት ነገር ትጋ፤ እነርሱ የሚያስተምሩህና የሚነግሩህ፥ ቃልንም ከልባቸው የሚያወጡ አይደሉምን? በውኑ ደንገል ረግረግ በሌለበት መሬት ይበቅላልን? ወይስ ቄጠማ ውኃ በሌለበት ቦታ ይለመልማልን?" (ኢዮብ 8፡9)። ክርስትና ያለ ትውፊት ምን ሊመስል እንደሚችል ከፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ሕይወት መማር ይቻላል። እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት በቅዱስ ትውፊት ላይ ያልተመሠረቱ በመሆናቸው በየዕለቱ እየተከፋፈሉና ዓይነታቸው እየበዛ ከመሄዱ አልፎ አንዳንዶቹ ፍጹም የክርስትና መልክ የሌላቸው ባዕድ አምልኮ /ከልት/ ወደ መሆን ተሸጋግረዋል። 

 

ቅዱስ ትውፊት በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን (Sacred Tradition)

የኦርቶዶክስና የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ከፕሮቴስታንት የሚለዩት ቅዱስ ትውፊትን በመቀበላቸው ነው። በኦርቶዶክስ ትምህርት የቤተ ክርስቲያን ሕይወት መሠረቱ የተጣለው፣ የሃይማኖታችን ያልተቋረጠና ያልተበረዘ ቀጥተኛ ጉዞ የሚረጋገጠው፣ እንዲሁም የአገልግሎታችን መንፈሳዊነቱ የተጠበቀ ይዘቱ የተሟላ የሚሆነው በቅዱስ ትውፊት ነው። ስለዚህም ሊቃውንት አባቶቻችን ቅዱስ ትውፊት "ድኅንነቱ በመንፈስ ቅዱስ የሚጠበቅ የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ነው" ብለው ያስተምራሉ።

 

ትውፊት ማለት በጽሑፍ ያልሰፈረ እንከን የሌለበት የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ሲሆን የክርስቶንና የቅዱሳን ሐውርያትን መልእክት የያዘ በመሆኑ ከልማድ የተለየ ብቻ ሳይሆን የተቀደሰም ነው። አሁን ካለው የቤተ ክርስቲያን ሕይወት አንጻር መጽሐፍ ቅዱስ ያለ ትውፊት በራሱ የተሟላ አይደለም። ይሁን እንጅ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ወንድሞቻችን በዮሐንስ ወንጌል ዮሐ 2031 የተጻፈውን በመጥቀስና "Sola Scriptura (Latin: "Scripture alone") የሚለውን የማርቲን ሉተር መርኅ በመከተል ለመዳን መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ በቂ ነው ብለው ይከራከራሉ።

 

ማስተዋል ካልጎደለ በቀር፣ "ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል" ከሚለው ዐረፍተ ነገር በፊት "ኢየሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ ሌላ ብዙ ምልክት በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ" (ዮሐ 20፡30) የሚለውን ቃል ልብ ብሎ መረዳት በተገባ ነበር። ቅዱስ ጳውሎስም "የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል" (2 ጢሞ 2፡16) በማለት ትውፊትን መሠረት አድርገው የተጻፉ መጻሕፍት አስፈላጊ መሆናቸውን ያረጋግጣል።

 

ቅዱስ ትውፊት የቤተ ክርስቲያን ሕግና የቅዱስ መጽሐፍ መሠረት ነው፤

የብሉይ ኪዳን ሕግ በሙሴ አማካኝነት ከመሰጠቱ በፊት ሕዝበ እስራኤል እግዚአብሔርን በትውፊት አማካኝነት ለብዙ መቶ ዓመታት ሲያመልኩ ኖረዋል። የእስራኤል እውነተኛ አምልኮና ሥርዓቱ በሙሴ ሕግ ከመጻፉ በፊት ስለ የብሉይ ኪዳን አባቶች ስለ መስዋዕት (ዘፍ 8፤20)፣ ስለ ቤተ እግዚአብሔርና ስለ አስራት በኩራት ሕግን ከእግዚአብሔር ቃል በቃል ተቀብለዋል። ለምሳሌ ቅዱስ ያዕቆብ በጉዞ ላይ እያለ ጌታ ሌሊት በራዕይ የቤተ ክርስቲያንን ምሥጢር ቁልጭ አድርጎ አሳይቶታል። እናም ሲነጋ ከመኝታው ተነስቶ “ይህ የእግዚአብሔር ቤት ነው” - "ይህም የሰማይ ደጅ ነው" በማለት ተንተርሶት ያደረውን ዲንጋይ አቁሞ በላዩ ላይ ዘይት አፍስሶበታል። በመቀጠልም "ከሰጠኸኝም ሁሉ ለአንተ ከአሥር እጅ አንዱን እሰጥሃለሁ" (ዘፍ 28፤17) በማለት በመንፈስ ቅዱስ የተነገረውን ሥራ ላይ ለማዋል ቃል ገብቷል። ይህ ሁሉ በአጠቃላይ የክርስትና ሃይማኖት አመሠራረትና የአምልኮታችን ሥርዓት ዘመን ያልተቆጠረለት በትውፊት ተጠብቆ የኖረ መሆኑን የሚያመለክት ነው።

 

በተመሳሳይ ሁኔታ ክርስቶስ ክርስትናን ሲያስተምር ክርስቲያኖችም ወንጌልን ሲማሩ በእጅ ላይ የተሰጣቸው በጽሑፍ የሰፈረ ማስረጃ አልነበረም። መሠረቱ ቅዱስ ትውፊት ነው። ከዚያም አልፎ እስከ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ እንዳሁኑ ባንድ ላይ የተጠረዘ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳልነበረ ይታወቃል። በዚህ መሠረት ከትውፊት ተነስቶ መልእክቶችን እንደጻፈ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ያረጋግጣል። "የከበርህ ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ከመጀመሪያው በዓይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት እንዳስተላለፉልን፥ በኛ ዘንድ ስለ ተፈጸመው ነገር ብዙዎች ታሪክን በየተራው ለማዘጋጀት ስለ ሞከሩ፥ እኔ ደግሞ ስለ ተማርኸው ቃል እርግጡን እንድታውቅ በጥንቃቄ ሁሉን ከመጀመሪያው ተከትዬ በየተራው ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ" (የሐዋ 1፡1)።

 

ትውፊት በቃል ደረጃ ሳለ ፍጹምና እንከን የሌለበት ሲሆን በጽሑፍ ላይ ሲሰፍር የፍጹምነት ባሕርይው አዳጋ ላይ እንደሚወድቅ ብዙ የሥነ-መለኮት ምሑራን ያትታሉ። መጽሐፍ ቅዱስ የትውፊት አንድ አካል ነው፤ እንደ አንድ የእምነት ማስረጃ ለንባብ የበቃውም በትውፊት አማካኝነት በመሆኑ የሚጎድሉት ነገሮች ብዙ ናቸው። አዳምና ሄዋን ሴቶች ልጆች እንዳላቸው በቅዱስ መጽሐፍ የተገለጸ ሳይኖር የአዳም ዘር ተባዝቶ ዓለምን እንደሞላ የምናስተምረው በቅዱስ ትውፊት አማካኝነት ነው። የሥላሴ አንድነት ሦስትነት፣ የሐዋርያት መሠረተ እምነት (Apostle's Creed) የጥምቀትና የቅዱስ ቁርባን ሥርዓት፣ በጠቅላላው የሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አፈጻጸም ፣ ዲያቆን፣ ቄስና ጳጳስ የምንላቸው የክህነት ደረጃዎች ወዘተ የተመሠረቱት በትውፊት አማካኝነት ነው። ስለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ በተሰሎንቄ የነበሩ ክርስቲያኖችን ሲመክር፣ "እንግዲያስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ጸንታችሁ ቁሙ፥ በቃላችንም ቢሆን ወይም በመልእክታችን የተማራችሁትን ወግ ያዙ" (2 ተሰ 2፡15)። እዚህ ላይ ሐውርያው "ወግ" በሚል ቃል  የገለጸው "ሰው ሠራሽ ልማድን" ሳይሆን በቅብብሎሽ የመጣ ሃይማኖታዊ ትውፊትን እንደህነ መገንዘብ ያስፈልጋል።

 

ቅዱስ ትውፊት መንፈሳዊ ውርስ ነው፤

ሳይበረዝና ሳይከለስ መሠረቱን ጠብቆ በቃል የሚተላለፍ እምነትና ትምህርት ትውፊት ይባላል። ይህም ትውፊት በአእምሮ የሚወረስ፣ በጽሑፍም የሚዳረስ፣ ብሎም በአደራነት ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ መንፈሳዊ ውርስ ነው። "እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው" (ሮሜ 10፡17) ተብሎ ተጽፏልና። ለምሳሌ ቅዱስ ጳውሎስ ሴቶች በማኅበር ጸሎት ጊዜ ራሳቸውን እንዲከናነቡ ያዘዘው በብሉይ ኪዳን ሕግ ያልተጻፈ ሕግ በራሱ መደንገግ ፈልጎ ሳይሆን በትውፊት ስላገኘው ነው (1ቆሮ 11፡5)። እንዲሁም ሐዋርያው ይሁዳ ቅዱስ ሚካኤል ከዲያብሎስ ጋራ ስለ ሙሴ ሥጋ በተከራከረ ጊዜ "ጌታ ይገስጽሕ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም" (ይሁዳ 89) ይላል። ይህ ቃል በትውፊት የተገኘ ነው እንጅ በየትኛውም የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ አልተጻፈም።

 

ስለዚህ ትውፊትን የማይቀበሉ አብያተ ክርስቲያናት ብዙ ነገር የጎደላቸው መሆኑን በቀላሉ መረዳት ይቻላል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ቅዱስ ጢሞቴዎስን ሲመክር "አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፥ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና" (2ጢሞ 3፡14) ካለ በኋላ "ብዙ ሰዎች የመሰከሩለትን ከእኔም የሰማኸውን ሌሎችን ደግሞ ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች አደራ ስጥ" (2 ጢሞ 2፡2) በማለት ይደመድማል። ይህ ዓይነቱ ተወራራሽ ትምህርት ቃል በቃል የሚተላለፍ እንጅ በጽሑፍ ላይ የሰፈረ እንዳልነበረ መገንዘብ ያስፈልጋል።


በተጨማሪም ቅዱስ ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለነበሩ ክርስቲያኖች "እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ" (1ቆሮ 15፡3) በማለት በክርስቶን ማመንን በትውፊት መልክ እንዳስተላለፈላቸው ገልጾ እነርሱም ይህን አክብረው በመጠበቃቸው እንዲህ ሲል ያመሰግናቸዋል። "አሳልፌ እንደ ሰጠኋችሁ ወግን ፈጽማችሁ ስለ ያዛችሁ አመሰግናችኋለሁ" (1ቆሮ 11፡2)።


ትውፊታዊ ውርስ ሳይዛባና ሳይበረዝ ይጠበቅ ዘንድ የግድ ነው

ክርስቲያኖች ይልቁንም የቤተ ክርስቲያን አባቶች በቃል የተላለፈ ክርስቲያንዊ ትውፊት በልማድ ሳይበረዝ ለትውልድ እንዲተላለፉ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው። ቅዱስ ትውፊት በሰው ልማድ የመዋጥ አዳጋ ሊያጋጥመው እንደሚችል "የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል" (ማቴ 15፡9) ሲል ጌታ የተናገረው ቃል ያመልክታል።

 

የጌታ አገልጋይ ቅዱስ ጳውሎስም ስለዚህ ሲጽፍ "እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ" (ቆላ 2፡8)። "በጌታ በኢየሱስ የትኛውን ትእዛዝ እንደ ሰጠናችሁ ታውቃላችሁና" (1ተሰ 4፡2) በማለት አገልጋዮችን ያስጠነቅቃል። በተጨማሪም ይኸው ሐዋርያ፦ "ወንድሞች ሆይ፥ ከእኛ እንደ ተቀበለው ወግ ሳይሆን ያለ ሥርዓት ከሚሄድ ወንድም ሁሉ ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን" (2 ተሰ 3፡6)። "ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን" (ገላ 1፡8) ይላል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚፈጸሙ የአምልኮት ሥርዓቶች ሁሉ ሐዋርያዊ ትውፊታቸውን ጠብቀው ለትውልድ ይተላለፉ ዘንድ በቀኖና ወይም በውሳኔ የታሰሩ እንዲሆን የሚያስፈልገው ትውፊትን ከሰርጎ ገብ ልማድ ለመለየት እንዲቻል ነው።

 

የአባቶች ምስክርነት

ቅዱስ ቀሌምንጦስ (88-97)

"የሕግ ልዕልና ተዘመረ፣ የነቢያት ጸጋ ተገለጠ፣ የወንጌል እምነት ተመሠረተ፣ የሐዋርያት ትውፊት ተጠበቀ፣ የቤተ ክርስቲያን ክብር ክፍ ከፍ አለ።"

 

ቅዱስ አይራኒዮስ (180-200)

"ቤተ ክርስቲያን ምንም እንኳን በዓለም ላይ የተበተነች ብትሆንም በአንድ ቤት እንዳለች አድርጋ የተቀበለችውን እምነትና ትምህርት በጥንቃቄ ትጠብቃለች። እነዚህንም የእምነት መርሆዎች……ለአንድ ወር እድሜ እንደተቀበለች አድርጋ ታውጃለች፣ ታስተምራለች፣ ሳይዛቡ ለትውልድ እንዲተላለፉ ታደርጋለች። ምንም እንኳን የዓለም ቋንቋ የተለያየ ቢሆንም የትውፊት አመጣጡና መሠረቱ አንድ ነውና።"

 

ቅዱስ አትናትዮስ (296-373)

"ነገር ግን ወንድሞች እዚህ ላይ ዋናው ነጥም ምንድር ነው!! ከመጀመሪያው ጀምሮ የነበረውን ጌታ ለቤተ ክርስቲያን የሰጣትን፣ ሐዋርያት ያስተማሩትን በአባቶች ዘንድ ተጠብቆ የኖረውን እምነት፣ ትምህርትና ትውፊት እናስታውስ። ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በእነዚህ ላይ ነውና። ማንም እነዚህን አክብሮ ባይዝ ክርስቲያን ተብሎ ሊጠራ አይገባውም።"

 

ቅዱስ ኤሚፋንዮስ (315-403

"ሁሉም መለኮታዊ ቃላት በምሳሌ የሚተረጎም አንድምታዊ ሐተታ እንዲኖራችው የግድ አያስፈልግም። የእያንዳንዱን ፍችና ትርጉም ለማወቅ የጠለቀ ሐሳብና ግንዛቤ ያስፈልጋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የትውፊትን አጠቃቀም መገንዘብ ይበጃል። ሁሉም የተነገረው ቃል ሁሉ ከቅዱስ መጽሐፍ የተገኘ አይደለምና። ቅዱሳን ሐዋርያት አንዳንድ ቃላትን ከቅዱስ መጽሐፍ አንዳንዶችን ደግሞ ከትውፊት ነውና ያስተላለፉልን።"

 

ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም (315-386)

"ትውፊታትን ሳታፋልስ ጠብቅ፤ ሰውነትህን ከክፋትና ከኃጢአት ተከላከል፤ ራስህን ከቅዱስ ቁርባን አታርቅ።"

 

"ኦርቶዶክስ - እውነተኛ የሕይወት መንግድ"

ክብር ለአምላካችን ይሁን፤ የቅዱሳን ረድኤትና በረከት አይለየን፣ አሜን

ይቆየን

 

 

ቀሲስ ዘመነ ደስታ

ሳን ሆዜ ካሊፎርንያ