የአውጣኪ የኑፋቄ ትምህርት በኢትዮጵያ ኦ.ተ. ቤተ ክርስቲያን

 

 ማሳሰቢያ፦ በዚህ ወቅት ከወትሮው በተለየ መልኩ ደጋግመን መልእክቶችን የምናስተላልፍበት ምክንያት ፌስ ቡክ ላይ የመጻጻፍ ሱስ ኖሮብን ወይም ግለሰቦችንና ድርጅቶቻቸውን ለመቃወም ወይም ዝነኝነትን ፈልገን አይደለም። እየተላለፈ ያለው የተዛባ ትምህርት የቤተ ክርስቲያናችንን ሕይወት የሚጎዳ በመሆኑ ሰምቶ ዝም ማለት ስለማይገባ ነው እንጅ። 

 

በዚህ ጽሑፍ አውጣኪ ማን ነው? ትምህርቱን ምን ይመስላል? በዘመናችን በማኅበር የተደራጁ ወጣቶችና ቀሳውስቶቻቸው የአውጣኪን እምነት ነው የሚከተሉት መባሉ ትክክል ነው ወይ? የሚሉትን  ነጥቦች እናያለን።

 

የአውጣቂ ማንነት ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ አንጻር

አውጣኪ እ.አ.ዘ 380-456 ዓመተ ምህረት በቁስጥንጥንያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የአንድ ገዳም አበ-ምኔት የነበረ፣ ለኦርቶዶክሳዊት ዕምነት በእጅጉ የሚቀና ነገር ግን ብዙ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የሌለው ሽማግሌ ቄስ ነበር።

"መሰናክል ግድ ሳይመጣ አይቀርም፥ ነገር ግን መሰናክሉን ለሚያመጣው ወዮለት (ሉቃ 17፡1) ሲል ጌታ እንደተናገው የአጋጣሚ ሆነና አውጣኪ በክህደት ትምህርቱና ነገር በማወሳሰቡ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ለኬልቄዶን ጉባኤ መካሄድና ለቤተ ክርስቲያን ከሁለት መከፈል ምክንያት የሆነ ሰው ነው።

 

     በዘመኑ የነበረው መናፍቅ ፓትርያርክ ንስጥሮስ ለክርስቶስ ሁለት አካላት ሁለት ባሕርያት አሉት በማለት ሰው የሆነውን አምላክ ከሁለት በመክፈሉና ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ ሰብዕ እንጅ ወላዲተ አምላክ ልትባል አይገባም በማለቱ "የተዋሕዶ ማኅተም" እየተባለ በሚጠራው በቅዱስ ቄርሎስ መሪነት በ431 ዓ.ም  በኤፌሶን ጉባኤ ተደርጎ ተወግዞ ከቤተ ክርስቲያን አንድነት ተልይቷል። በዚህ ጊዜ አውጣኪ የቄርሎስ ትምህርት ደጋፊና ዋና የተዋሕዶ እምነት አርበኛ መስሎ ሲራመድ ነበር። ይሁን እንጅ የቅዱስ ቄርሎስትን ትምህርት በአግባቡ ለመረዳትና ለማስረዳት የጠለቀ የሥነ-መለኮት ትምህርት የሌለው ተራ ካህን በመሆኑ ከንስጥሮስ ሞት በኋላ በንስጥሮስ ደጋፊዎችና በተዋሕዶ እምነት ተቀባዮች መካከል ያለው ክርክር እየጦፈ ሲመጣ አውጣኪ በቄርሎስ ትምህርት ላይ የሚሰጠው ማብራሪያ መስማሩን እየሳተ መጣ። የንስጥሮስ ትምህርት ዋና ችግሩ "በተዋሕዶ አምላክ ሰው ሰውም አማልክ ሆነ" የሚለውን ትምህርት አምኖ መቀበል ስለነበር የአውጣኪ ትኩረት ደግሞ ለክርስቶስ መለኮታዊነት ትኩረት መስጠትና የቅድስት ድንግል ማርያምን ወላዲተ አማላክነት ማረጋገጥ ነበር። ይሁን እንጅ አውጣኪ "አንድ አካል አንድ ባሕርይ" የሚለውን የቅዱስ ቄርሎስ ትምህርት የተረዳው በሌላ መንገድ ነበር። እናም ፍጹም መስመር አልፎ በመሄድ ክርስቶስ ሰው በሆነ ጊዜ መለኮት የሥጋን ባሕርይ ውጦ አጥፍቶታል ብሎ በማስተማር የክርስቶስን ትስብዕቱን (ፍጹም ሰው መሆኑን) ካደ። ይህም በቤተ ክርስቲያናችን አስተምሕሮ "የአንድ ገጽ" ትምህርት (Monophysitism) ይባላል። የቅዱስ ቄርሎስ ትምህርት Miaphysitism አንጅ Monophysitism አይባልም። Miaphysitism "ለክርስቶስ አንድ አካል አንድ ባሕርይ አለው" ማለት ሲሆን ይህም መለኮትና ትስብዕት በልዩ የረቀቀ ተዋሕዶ ከሁለት አካላት አንድ አካል ከሁለት ባሕርያት አንድ ባሕርይ መሆናቸውን የሚያመለክት ነው። የአውጣኪ የክህደት ትምህርት ግን Monophysitism ይባላል። ምክንያቱም Monophysitism ማለት የሥጋ ባይህርይ በመለኮታዊ ባሕርይ ተተክቶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ማለት ነውና።

 

    አውጣኪ ከዕውቀት ማነስ የተነሳ የፈጠረው ክህደት የቤተ ክርስቲያንን ቀጥተኛ አስተምህሮ ከማዛባት አልፎ አባቶችንም ማወናበዱ አልቀረም። ይህ አዲስ ትምህርት በቁስጥንጥንያ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ሲሰማ የቁስጥንጥንያው ሊቀ ጳጳስ ፍላቪያን በአካባቢው ያሉ ጳጳሳትን ሰብስቦ በ448 ዓ.ም. በውግዘት ከ30 ዓመታት በላይ በአበ-ምኔትነት ካገለገላት ቤተ ክርስቲያን እንዲለይ አደረገው። በዚህ ጊዜ አውጣኪ የልቡን ከልቡ አድርጎ የቅዱስ ቄርሎስትን ትምህርት ስላስተማርኩ በውግዘት ከቤተ ክርስቲያን ተለይቻለሁና እንደተለመደው በእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን መሪነት ዓለም-አቀፍ ጉባኤ ተጠርቶ ይታይልኝ እያለ መወትወት ጀመረ።

 

    እዚህ ላይ ከቅዱስ ቄርሎስ ሞት በኋላ የእስክንድርያን ቤተ ክርስቲያን በፓትርያርክነት ይመራ የነበረው ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በጣም ተሸውዷል የሚሉ ሊቃውንት ብዙ ናቸው። ምክንያቱም የአውጣኪን ተለዋዋጭ ባሕርይ ሳያውቅ በ449 ዓ.ም. ጉባኤ አድርጎ አውጣኪን ከውግዘቱ እንዲፈታና ወደ ቤተ ክርስቲያን አንድነት እንዲመለስ ማደረጉ ነው። በዚህ ጉባኤ የቁስጥንጥንያው ሊቀ ጳጳስ ፍላቪያን አልተገኘም፤ ምክንያቱም እርሱ ያወገዘው ማናፍቅ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሊመለስ ይችላል የሚል ጥርጣሬ ስለነበረው ነው። የሮሙ ሊቀ ጳጳስ ሊዮንም አልተገኘም። ነገር ግን "ለክርስቶስ አንድ አካል ሁለት ባሕርያት አሉት" የሚል ጽሑፍ አስይዞ መልእክተኞችን ልኳል። "የልዮን ጦማር" ካቶሊኮችና የምሥራቅ ኦሮቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት እስከ አሁን ድረስ የሚመኩበት የእምነታቸው መሠረት የሆነ መልእክት ነው። ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ይህን ጽሑፍ "ጦማረ-ልዮን" በጉባኤ እንዲነበብ አላደረገም። ከንስጥሮስ ትምህርት ብዙም ያልራቀ ሆኖ አግቶታልና። በዚህም ምክንያት ምዕራባውያን ቅዱስ ዲዮስቆሮስንና የእስክንድርያን ቤተ ክርስቲያን "Monophysite" የአንድ ገጽ እምነት አራማጅ ብለው አውግዘዋል። ቅዱስ ዲያስቆሮስና ተከታዮቹም ሊዮንና ተከታዮቹን በዚች ጽሑፍ ምክንያት "ንስጥሮሳዊያን" ብለው አውግዘዋቸዋል።

 

    ቅዱስ ዲዮስቆሮስ አውጣኪ መናፍቅ መሆኑን ተገንዝቦ በኋላ እንደገና ያወገዘው ቢሆንም በሁለተኛው የኤፌሶን ጉባኤ በ448  ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመለስ ማድረጉና ይህንንም ተከትሎ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የተፈጸመው ወደ ልዩነት የሚያመራ መወጋገዝ የእስክንድርያን ቤተ ክርስቲያን ከዓለም-አቀፍ የቤተ ክርስቲያን መሪነት ለማውረድ ሲጥሩ ለነበሩ ምዕራባውያን ምቹ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል። ከዚህ በኋላ ከፖለቲካው ጋራ ተጣብቀው በእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ላይ በማሴር ያለ አንዳች ምክንያት የኬልቄዶንን ጉባኤ እንዲጠራ አድርገዋል። በኬልቄዶን ጉባኤ ቅዱስ ዲዮስቆሮስን መናፍቅ ለማለት ሞክረው ነበር። ነገር ግን ከመምህሩ ከቅዱስ ቄርሎስ ያገኘውን ዕውቀት መሠረት አድርጎ የሚሰጣቸውን ምላሽ መቋቋም አልቻሉም። እናም በአልታዘዝ ባይነትና በሌላም ፖለቲካዊ መስመር ወንጅለው ከዓለም-አቀፍ የጉባኤ መሪነት ቦታውን ለቆ እንዲወርድና ጥርሶቹ እስከሚረግፉ ድረስ በጭካኔ እንዲደበደብ አድርገዋል። ሕይወቱም ያለፈው በግዞት ነው።

 

በቤተ ክርስቲያናችን በማኅበር የተደራጁ ወጣቶችን አውጣኪ የሚያስብላቸው መሠረታዊ ነጥቦች፤

በዘመናችን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ  በማኅበር የተደራጁ ወጣቶች ከአውጣኪ ጋር የሚያመሳስላቸውን ሦስት መሠረታዊ ነጥቦች በማንሳት የእነዚህ ወጣቶች እንቅስቃሴ ምን ያክል ለቤተ ክርስቲያን አደገኛ እንደሆነ ለማሰየት እሞክራለሁ።

 

(ሀ) መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ሳይኖራቸው በቀናኢነት መነሳሳት፣

(ለ) የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ማሳሳት፣

(ሐ) የክርስቶስን አምላክነት ያጎሉ እየመሰላቸው ፍጹም ሰውነቱን መካድ፣

 

(ሀ) መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ሳይኖራቸው በቀናኢነት መነሳሳት

አውጣኪ ለኦርቶዶክሳዊት እምነት ፍጹም የሚቀና ለዚያውም የገዳም አበ-ምኔት በመሆን ከ30 ዓመታት በላይ ያገለገለ አረጋዊ አባት ስለነበር ከቅዱስ ቄርሎስ ትምህርት ያፈነግጣል ብሎ የጠበቀ አልነበረም። እሱም የገባበት የክህደት ገደል ምን ያክል ጥልቅ መሆኑን አልተገነዘበም ነበር። ምክንያቱም የያዘው እምነት ትክክል ይመስለዋል፤ መሠረታዊ የሥነ-መለኮት ትምህርት አልነበረውምና። በዚህ ምክንያት ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ከውግዘቱ ፈትቶ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመለስ ካደረገው በኋላም እንኳን ጥፋቱን አምኖ ይቅርታ ሊጠይቅ አልቻለም። በማስተዋልና በእውቀት ላይ ያልተመሠረተ ቀናኢነት እልኸኛ እና አክራሪ ያደርጋል። በቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዚህ አቋማቸው ከመናፍቃን ጎራ ተቆጥረው በሊቃውንት ጉባኤ የተወገዙ ቡድኖች ብዙ ናቸው። ከእነዚህም መካከል ራሳቸውን የጻድቃን ማኅበር አድርገው የሚቆጥሩ በሮም ዘመነ መንግሥት በሰይፍ ተገደው ሃይማኖታቸውን የለወጡ ክርስቲያኖች ቆስጠንጢኖስ ከነገሠ በኋላ ሰላም ሲፈጠር ወደ ቤተ ክርስቲያን በንስሐ እንዳይመልሱ የከለከሉ Novatianists እና Donatists የተባሉትን የእምነት ቡድኖችን መጥቀስ ይቻላል። ዛሬም በተመሳሳይ ሁኔታ የዚህ ማኅበር አባላት እምነታቸውን ያጠበቁ እየመሰላቸው ብዙ ወጣቶችን ከቤተ ክርስቲያን እያራቁ ይገኛሉ።

 

    በይበልጥም ደግሞ ከሰንበት ትምህርት ቤት ተነስተው ቅስናን የተቀበሉና ራሳቸውን ለትልቅ ማዕርግ ያዘጋጁ የማኅበሩ አባላት ቅናታቸው በመሠረታዊ ትምህርት ያልተደገፈ በመሆኑ እየሄዱበት ያሉት መስመር የተሳሳተ መሆኑን እንኳን ለማየት ዕድል አላገኙም።

 

    ከሰሞኑ በቲፎዞ ብዛት እውነትን ለማስለወጥ ሲደረገ የነበረው ርብርብ የሚያመለክተው ይህንኑ ነው። ብፁዕ አቡነ በርናባስ መድኃኔዓለም ክርስቶስ በፈሰሰው ደሙ አስታርቆናል በማለት ያስተማሩትን ትምህርት ተቃውመዋል። ይህ ትምርህት በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በሊቃውንት ትምህርት በግልጽ የተብራራ በመሆኑ አምታትቶ ለማለፍ ያስቸግራል። ስለዚህም ይደግፉናል ብለው የተማመኑባቸው የተባ ብዕር ያላቸው ጸሐፊዎቻቸው ሁሉ ትተዋቸው ገሸሽ ብለዋል። በይበልጥም ደግሞ በሀገር ቤት የሚገኙ ሊቃውንት "ይህ በሰንበት ት/ቤት አቅም የሚለካ አይደለም" በሚል በሳል አነጋገር አካሄዳቸውን ተችተውና የክርስቶስን አስታራቂነት ወይም አማላጅነት ደግፈው መልስ ሰጥተዋቸዋል። ይሁን እንጅ ለጊዜው ሐሳቡን የተቀበሉ መስለው ካደፈጡ በኋላ እንደገና ተመልሰው የአውጣኪን ክህደት መዝራት ጀምረዋል። ትምህርታቸው ከአውጣኪ ትምህርት ጋር ያለውን ቁርኝት በክፍል (ሐ) በዝርዝር እነመለከታለን።

 

    እነዚህ ሰዎች በጣም ግራ የገባቸው ናቸው። አንድ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ከዕብራይስጥና ከግሪክኛ የተተረጎመ መሆኑን በመዘንጋት የሀገር ፍቅርና ብሔራዊ ስሜት ያላቸው ለማስመሰል ግዕዝ እንጅ ግሪክኛና ዕብራይስጥን መጥቀስ አይገባም፤ የአረማውያን ቋንቋዎች ናቸው ይላሉ። በግዕዝ የተጻፈውን የሊቃውንት ትምህርት ማለትም የእነ ቅዱስ ቄርሎስንና ዮሐንስ አፈወርቅን መልእከት ሲያቀርቡላቸው ደግሞ ለመቀበል ይቸገራሉ። የሊቃውንቱን ትምህርት ለመቀበል በጎ ፍላጎት ካላቸው ከዚህ በፊት ያቀረብኩትን እንድገና እጽፍላቸዋለሁ።

· ሊቁ ቅዱስ ቄርሎስ:- "ወእምድኅረ ኮነ ሰብአ ተሰምየ ብዕሴ ወኢየሱስሃ፣ ወታቦተ ወአራቄ ወበኩረ ለዘሰከቡ" "ሰው ከሆነ በኋላ ብእሲ፥ መሲሕ፥ ኢየሱስ፥ ታቦት፥ አስታራቂ፥ ለሙታን በኩር…ተባለ" (ሃይማኖተ አበው ም 81 ቁ 8 ገጽ 338)።

· ቅዳሴ ማርያም፦ "አንቃዕደወ ሰማየ ኅበ በቡሁ ወአስተምሐረ ወላዲሁ ወአማኅጸነ አርዳኢሁ ከመ ይዕቀቦሙ እምኩሉ እኩይ" "ወደ ሰማይ ወደ አባቱ ቀና ብሎ አየ፤ ወላጅ አባቱንም ማለደ፤ ደቀ መዛሙርቱንም ከክፉው ሁሉ ይጠብቃቸው ዘንድ አደራ አስጠበቀ" (ቅዳ ማር ቁ 113)።

· ሊቁ ቅዱስ ቄርሎስ:- "ወሰአሎ ለአብ ያኅልፍ መዐተ ዘረከበነ፣ ከመ ዘለሊሁ ይኄልቁ ስእለተ ሎቱ እስመ ውእቱ ነስአ አምሳሊነ ከም ይስአሎ ለአብ በእንቲአነ" " "እርሱ ለራሱ ልመናን የሚሻ መስሎ ከጥንት ጀምሮ ያገኘንን ፍዳ ከእኛ ያርቅ ዘንድ አብን ማለደው። እንደገና ደግሞ እንዲያስበን ከእርሱም እንዳይለየን ስለእኛ አብን ይማልደው ዘንድ ባሕርያችንን ነስቷልና"  (ሃይ አበ ም 79 ክፍል ቁ 38)።

· ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ:- "እርሱ አንድ ባይሆን ኖሮ የማይሞት ባልሆነም ነበር። የኦሪቱ ካህናት ግን የሚሞቱ ስለሆኑ ብዙ ናቸው። እንደዚሁም ሁሉ ይህ አንድ የሆነው የማይሞት ስለሆነ ነው። ሐዋርያው በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ዘወትር ሊያድናቸው ይችላልና ለዘላለም የማይሞት ሕያው ስለሆነ፤ ስለእነርሱም ይማልድላቸዋል። ወዳጅ ሆይ፤ ይማልድላቸዋል ብሎ ያለው ሰው ስለመሆኑ እንደሆነ ተረዳህን? ሊቀ ካህናት በመሆኑ ያን ጊዜ ይማልድላቸዋል አለ . . . ለዘላለም ሕያው ስለሆነ ለዘወትር ያድናቸው ዘንድ ይችላልና አለ። ከእርሱ በኋላም የሚተካ የለም" (የዮሐንስ አፈወርቅ 13ኛ ድርሳን ቁ 129-131፤ 135-136)።

· ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ:- "እስመ ውእቱ ይተነብል በእንቲአነ" "እርሱ ስለኛ ማልዶልናልና የምናምንበት ሊቀ ካህናት (አስታራቂ) አለው ዮሐ 16፡1-26" (ሃይ አበ ም 63 ክፍል 2 ቁ 26)።

·   ነቢዩ ኢሳይያስ፦ "ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ" (ኢሳ 53፡12)።

 

(ለ) የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ማሳሳት

አውጣኪ ለቅዱስ ቄርሎስ እውነተኛ ትምህርት ራሴን አሳልፌ እሰጣለሁ እያል ነገር ግን በልቡ ባዕድ ሐሳብ ይዞ በመቅረብ ቅዱስ ዲዮስቆሮስን ሊያሳስተው ሞክሯል፤ ርቆ ሳይሄድ ነቃበት እንጅ። እነዚህም ወጣቶች ኤ ቢ ሲ ዲ ስለ ቆጠሩ አባቶቻችን ለቤተ ክርስቲያን የላቀ ሥራ የሠሩ እየመሠላቸው ያለገደብ እንዲንቀሳቀሱ ዕድል ሰጥተዋቸዋል። የ25 ዓመታት የሥራ ውጤታቸው ሲመዘን ግን ትርፉ ኪሳራ ነው። ሚሊዮኖችን ከተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አውጥተው አባረዋል። አባቶችን ከአባቶች ጋር ያጋጫሉ፤ ቤተ ክርስቲያናችንን ከእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያንና ከሌሎችም አሐት አብያተ ክርስቲያናት ጋራ ሊነጣጥሏት ጠንክረው ይታገላሉ። ከዚህ በፊት መሪዎቻቸው ከአቡነ ሺኖዳ ሳይቀር እየሄዱ ደጅ ሲጠኑ ነበር። መጻሕፍቶቻቸውንም ወደ አማርኛ በመተርጎም ለእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ያላቸውን አድናቆት ሲገልጹ ኖረዋል።

አሁን በአባይ ግድብ ምክንያት አለመግባባት ከተፈጠረ ወዲህ ደግሞ የነበረውን አድናቆታቸውን ቀዝቀዝ ከማድረግ አልፎ በቃላት መጎንተል ጀምረዋል።

 

    ለምሳሌ በቅርቡ የኢትዮጵያ ኦ.ተ. ቤተ ክርስቲያን የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ጋር የእምነት፣ የሥርዓትና የሥነ-ምግባር ጉድለት እንዳለባት አስመስለው ለሲኖዶስ አቅርበው ካወያዩ በኋላ "የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋራ ያላትን የሃይማኖት አንድነት ለትመረምር ነው" በሚል ቃል የቤት ሥራቸውን እየሠሩ መሆናቸውን በድኅረ ገጻቸው ይፋ አድርገዋል። ለዚህ ጽሑፍ መልስ "አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ አወጣ" በሚል ርዕሰ በቀሲስ አስተርአየ ሰፊ መልስ የተሰጠ በመሆኑ አንብቦ መረዳት ይጠቅማል።

 

    ከሁሉም በላይ የሚከፋው ደግሞ እንግዳ ትምህርት ይዘው በመምጣት አባቶችን እያሳሳቱ መሆኑ ነው። አንዳንድ በሀገር ቤት በሚገኘው ሲኖዶስ ስር ያሉ ያልገባቸው አባቶች የዚህን ማኅበር ጩኸት ማስተጋባት ጀምረዋል። የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ከሚፈታተኑ ወገኖች ጋር ከማበር አብሮ መሥራት የመረጥ ነበር።  ይሁን እንጅ በስደት ከሚኖሩ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ማንም የእነሱን የቃላት ጦርነት ፍርቶ እውነትን ከመመስከር ወደ ኋላ የሚል እንደሌለ ሊገነዘቡ ይገባል። እውነት ተቀብሮ አይቀርም፤ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትም ሞተው አላለቁም። 

  

(ሐ) የክርስቶስን አምላክነት ያጎሉ እየመሰላቸው ፍጹም ሰውነቱን መካድ፣

በቅርቡ የብፁዕ አቡነ በርናባስን ትምርህት ለመቃወም ከዚህ ማኅበር አባላት አንዱ ካህን ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልዕክቱ "ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ" (ዕብ 5፡7) ሲል የተናገረውን ሲያብራሩ "በንባቡ ጸሎትና ምልጃ የተባለው፡-“አማለደ፤ ለማለት ሳይሆን፥እንደ ላምና እንደ በግ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረቡን እንደሆነ ማስተዋል ይገባል" በማለት ጸሎትም ሆነ መስዋዕት የምልጃ ክፍል መሆናቸውን ላለመቀበል የተለየ ትርጓሜና ሐተታ ውስጥ ገብተው እናያለን። በመቀጠልም እኝህ ካህን ሲጽፉ እጠቅሳለሁ፣ "ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- በመዋዕለ ሥጋዌው (በተዋህዶ ሰው በሆነበት ዘመን) ለአብነት (ምሳሌ ሊሆነን) ያደረገውንና ለድኅነታችን ብሎ የፈጸመውን መለየት ያስፈልጋል። ብዙዎች እነዚህ ሁለት ነገሮች እየተደባለቁባቸው ነው፥ ዛሬም ያማልዳል፤ የሚሉት። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- እከብር አይል ክቡር፥ እጸድቅ አይል ጻድቅ ሲሆን፡- የጾመው፥ የጸለየው፥ የሰገደው፥ ለእኛ፡- አብነት (ለበጎ ነገር ሁሉ አርአያና ምሳሌ) ሊሆነን ነው። ማቴ፡፬፥፪፣ ሉቃ፡፳፪፥፵፩ ፣ዮሐ፡፲፩፥፵፩" ብለዋል።

 

    በጣም የሚገርመው እኝህ ካህን ጌታ የጸለየው ለአርአያነት ነው በማለት አሳንሰው አቅርበዋል። "አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው" (ሉቃ 23፡34) ብሎ መጸለይ የአርአያነት ሥራ ነው እንዴ? ትክክል አይደለም። በሰውነቱ ለዓለም ዕርቅን ያወጀበት፣ የአባቱን ስም በመጥራት ብቻውን እንዳልሆነና ይልቁንም ለአባቱ ፍጹም ታዛዥ መኖኑን ያስመሰከረበት፣ መዳን በሦስቱ አካላት በጎ ፈቃድ የሚፈጸም መሆኑን ያረጋገጠበት የትህትና ሥራ ነው። "እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ ፍርዴም ቅን ነው፥ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና" (ዮሐ 5፡30)።

 

    ዋና ነጥብ "እከብር አይል ክቡር፥ እጸድቅ አይል ጻድቅ" በሚል አነጋገር የክርስቶስን መለኮታዊ ክብሩን ያጎሉ እየመሰላቸው በሰውነቱ የሠራቸውን ሥራዎች ሁሉ ለአምላክነቱ ጠቅልሎ መስጠት ነው አውጣኪ የሚያስብለው። ለምሳሌ በምሥጢረ ሥጋዌ የሥነ-መለኮት ትምህርታችን መድኃኔዓለም ክርስቶስ "ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ" ነው ብለን ነው የምናምነው። ፍጹም ሰው መሆኑና ፍጹም አማልክ መሆኑ በድኅነት ሥራ ላይ ተቃርኖ የላቸውም። ዓለምን ከራሱ፣ ከአባቱና ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ሊያስታርቅ ራሱን መስዋዕት አድርጎ ሲያቀርብ እንደ ፍጹም ሰውነቱ ነው። ሲጸልይም እንደ ፍጹም ሰውነቱ ነው። የሞተውም ፍጹም ሰው ስለ ሆነ ነው፤ ራሱን ማዳን ተስኖት ግን አይደለም። ራሱ ያቀረበውን መስዋዕት ሲቀበል ደግሞ እንደ ፍጹም አምላክነቱ ነው። አቀባባይ አያስፈልገውም። ስለዚህ በፍጹም ሰውነቱ የሠራቸውን የአስታራቂነት ሥራዎች ለአርአያነት ብቻ የተደረጉ አስመስሎ ማለፍ የሰው ልጆችን ድኅነት ከንቱ ያደርጋል። በእርግጥ ከሚፈጽሙት ግዳጅ በስተጀርባ አርአያነታቸው ጎልቶ ይታያል። ቅዱስ ቁርባንን የዘለዓለም ሥርዓት አድርገን መቀጠላችን ከእነዚህ አንዱ ምሳሌ ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ለአርአያነት የሠራቸው በሰውነቱ ጎልተው የታዩ በጎ ምግባራት አሉ፤ ትዕግስት፣ ጠላትን መውደድ፣ ክፉ ሲናገሩ ዝምታን መምረጥ፣ ወዘተ። ሆኖም እዚህ ላይ እየተነጋገርንባቸው ያሉት የምልጃና የአስታራቂነት ሥራዎች ግን ለቤዛነት የሠራቸው ሥራዎች ናቸው።

 

     ሌላው እኝህ ካህን ከተናገሯቸው ቃላት አንዱ "አብ ሾመው ለማለት ሳይሆን" በሚል ግልጽ ቋንቋ እኛ ለማዳን የተላከ ሊቀ ካህናት መሆኑን ያስተባበሉበት ትምርህት በዓይነተኛነት ይጠቀሳል። ይህ በዳኅጸ ልሳን የተነገረ ተራ ቃል ተደርጎ የሚታለፍ ሳይሆን ነገር መለኮትን የሚያዛባ ታላቅ የዶግማ ሕጸጽ ነው። አውጣኪ የሚያስብለውም እንዲህ ዓይነቱ ንፍቀት ነው። ክርስቶስ ራሱን የሾመ ሊቀ ካህናት አይደለም። የተሾመው በአባቱ ፈቃድ በመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ ነው። ይህን አስመልክቶ ነቢዩ ኢሳይያስ ሲጽፍ "መንፈሰ እግዚአብሔር ላዕሌየ ዘቀብአኒ ዘበእንቲአሁ አስተፍሥሆሙ ለነዳያን ፈነወኒ" (ኢሳ 61 1) ብሏል። ይህም ማለት ስለሱ ነዳያን ትሩፋንን ደስ አሰኛቸው ዘንድ በኔ ያደረ መንፈሰ ረድኤት ላከኝ። አንድም "በኔ ሕልውና ባለ መንፈስ ቅዱስ ያዋሐደኝ እግዚአብሔር አብ ምዕመናንን አስተምራቸው ዘንድ ላከኝ"። "ወእፈውሶሙ ለቁስላነ ልብ" በቁስለ መከራ የተያዙትን አድናቸው ዘንድ፤ "ወእስብክ ሎሙ ግዕዛነ ለፄዋውያን" ለተማረኩት ነጻነትን አስተምራቸው ዘንድ ማለት ሚጠትን አስተምራቸው ዘንድ ላከኝ። "ወይርአዩ እውራን" እውራነ ልቡና እስራኤል ያዩ ዘንድ ላከኝ። የሐዲስ ኪዳን ሊቃውንትም ይህንኑ የነቢዩን ቃል በሉቃስ 4፡ 16-22 በተመሳሳይ መንገድ ተርጉመውታል። በተጨማሪም ቅዱስ ጳውሎስም እንዲህ ብሏል። "ዘቀብኦ እግዚአብሔር መንፈሰ ቅዱሰ ወኃይለ" (የሐዋ 10፡38)፣ "እግዚአብሔርነቱ ኃይሉ ሕይወቱ በሚሆን በመንፈስ ቅዱስ የመረጠው የሾመው"፣ "ውእቱ መጽአ" "ከገሊላ ወደ ይሁዳ በመምህርነት መጣ" "ወረድኦሙ ለእለ ይተዔገሎሙ ሰይጣን" ሰይጣን ድል አድርጓቸው የነበሩትን ረዳቸው"

 

     በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሳይሾምና ሳይላክ ሊቀ ካህናት ሆኖ ሊያገለግል የሚችል ሰው የለም። ሊቀ ካህናት መልከጼዴቅ በክርስቶስ የተመሰለበት ምክንያት የዘር ኃረጉ ሳይጠቀስ ክህነት በዘር ኃረግ ከሚተላለፍበት ከአይሁድ ሕግ ውጭ ዘለዓለማዊ ካህን ሆኖ ስለተሾመ ነው። እናትና አባቱ አለመጠቀሳቸውና የአሟሟቱ ሁኔታ አለመገለጹ የክህነቱን ዘለዓለማዊነት ያረጋግጣል። ይህ ማለት ግን እናትና አባቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ስላልተጠቀሱና ማን እንደሾመው በዝርዝር ስላልተገለጸ ሳይቀባ ራሱን የሾመ ነው ማለት አይደለም። የሐዲስ ኪዳንም ሆነ የብሉይ ኪዳን ሕግና ሥርዓት መሥራች ክርስቶስም በለበሰው ሥጋ በሊቀ ካህናትነት ሲገለጽ በዚሁ ሥርዓት ተሹሞና ተልኮ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ጌታ ራሱ ሲናገር "አንተ እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ" (ዮሐ 17:20) ብሏል።   

 

     የጸረ-ተሐድሶ ጋጋታ ውጤቱ ይኸው ነው። ፕሮቴስታንቶች ክርስቶስን የዘለዓለም አማላጅ አድርገው ዛሬም እየወደቀና እየተነሳ እንደሚጸልይ ወይም እንደሚማልድ ያስተማሩትን የተሳሳት ትምህርት ለመቃወም ተብሎ ያለ ችሎታ የወልድን አምላክነት ለመከላከል መስመር የሳተ ትንታኔ ውስጥ መግባት እንዲህ ሳይታሰብ የክህደት ገድል ውስጥ ይከታል።  

 

     የምልጃ ትምርህት አከራካሪ የሆነበት ዋናው ነጥብ ምልጃ ወይም አስታራቂነት የቤዛነት ሥራ ስለሆነና ይህ ትምህርት በሰው ልጆች ድኅነት ላያ ያለው አንድምታ የጎላ በመሆኑ ነው። አውጣኪን ተሳስቷል የምንለው የክርስቶስን የሰውነት ባሕርይ ክዶ የዓለም ድኅነት ተፈጸመ ለማለት በመሞከሩ ነው። አምላክ የመረጠው ብቸኛ መንገድ በብሉይ ኪዳን ይፈጸሙ የነበሩ የጸሎት፣ የምልጃና የአስታራቂነት ሥራዎችን ሠርቶ ራሱን እንከን የሌለበት መስዋዕት አድርጎ ሰውቶ ዓለምን ማዳነ ነው። ያ ባይሆን ኖሮ ሰው መሆን ባላስፈለገውም ነበር። በአጠቃላይ የምልጃን ትምህርት ለመቃወም ተብሎ በእኝ ካህን በኩል ይተላለፈው መልእክት መስመሩን የሳተ ነው። ክርስቶስ ለኛ ሲል በለበሰው ሥጋ የተቀበለው መከራ እንዳልተሰማው ያሳያል። "አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ" ሲል የጸለየውም ጸሎት በለበሰው ሥጋ ስቃይ ተሰምቶት ሳይሆን መከራ በደረሰባችሁ ጊዜ እንደዚህ ጽልዩ ለማለት የተደረገ ምሳሌ እንደሆነ ያመለክታል። አውጣኪ የሚያስብለውም ይኸው ነው። እንጸልይ።

 

የኢትዮጵያ አምላክ ለሁላችንም ማስተዋሉን ያድለን። የቅዱሳን በረከት አይለየን አሜን።

 

ቀሲስ ዘመነ ደስታ

ሳን ሆዜ ካሊፎርንያ