የክርስቶስ የቤዛነትና የአስታራቂነት ሥራ

የወቅቱ አንገብጋቢና አወዛጋቢ ርዕስ

 

መግቢያ፦ እየተሠራጨ ስላለው የተዛባ ትህምርትና መወሰድ ስለሚገባው እርምጃ

በዚህ ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን አስመልክቶ በኢንተርኔት ባስተላልፍኩት መልእክት በዚህ ዘመን ያሉ በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በወንጌላዊነት የተሰማሩ ሰባክያን ብቃትና ችሎታ ምን ድረስ እንደሆነ ለማሳየት ሞክሬአለሁ። ወንጌላዊያኑ ብቻ ሳይሆኑ ይህ ትውልድ በጠቅላላ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እምነት ላይ ያለው ዕውቀት ውስን በመሆኑ በጀሮው ሰምቶት የማያውቀው ለእርሱ አዲስ የሆነ የወንጌል ምሥጢር ሲፈልቅ ተደጋግፎ በመሄድ አንዱ ያለውን ሌላው ከማስተጋባት በቀር ከራሱ አመንጭቶ የሚሰጠው ምላሽ የለውም። ማጠፊያው ሲያጥረው ደግሞ መልሱ ስድብ ይሆናል። በብዙ ሃይማኖቶች ስለ እምነቱ በራሱ የሚተማመንበት ዕውቀት የሌለው ሰው በጣም ፈሪና ቶሎ ተናዳጅ ነው። በእኛም ቤተ ክርስቲያን ለምሳሌ "ኢየሱስ" የሚለው ቃል ሲሰማ የጴንጤዎች ስም እየመሰላቸው ደፍረው ለመናገር የሚፈሩ፤ ምልጃ ሲባል የሚደነብሩ ብዙ ናቸው። ኢየሱስ የሚለው ስም የዓለምን ገጽታ የለወጠ ዲያብሎስን የቀጠቀጠ ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው "እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም" ነው (የሐዋ 4፡12)። ነገር ግን ከአለማወቅ የተነሳ እንድንበት ዘንድ የተሰጠንን ስም ደፍረን ለመጥራት እንፈራለን።

 

        በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ የተዛባን ትምህርት አንብበንና ጠይቀን መስመር ማስያዝ ሲያቅተን እኔ ያልኩት ብቻ ነው ትክክል በሚል በማሳመንና በመተማመን ሳይሆን በአድማና በደጋፊ ብዛት በአሸናፊነት ለመወጣት የኃይል እርምጃ እስከ መውሰድ የደረሰ ጥፋት ሲፈጸም እንደኖረ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ሠለስቱ ምዕት (318 ሊቃውንት) አርዮስን ከማወገዛቸው በፊት ሰፊ ጊዜ ሰጥተው ባይከራከሩት ኖሮ ቤተ ክርስቲያን ርቃ ሳትሄድ በዚያ ዘመን በተከፋፈለች ነበር።  

 

       በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ድረስ አንዳንድ ከኅሊና በላይ የሆኑ ኦርቶዶክሳዊ ይዘት የሌላቸው ሰርጎ ገብ የትምህርት ዓይነቶች እንዳሉ ይታወቃል። እነዚህ ትምህርቶች የተለመዱ ቋሚ የዕምነት መግለጫ ለመሆን የበቁት ያለ አንዳች ፍርሃትና መሸማቀቅ በቃልም ሆነ በጽሑፍ ሲቃወሙ የኖሩ ሊቃውንት እየሞቱ ሲያልቁ መናፍቅ እባላለሁ በሚል ፍርሃት ደፍሮ የሚቃወም ባለመኖሩ የኃይል ሚዛኑ እያዘነበለ ስለመጣ ነው። በዘመናችን ራሱን የቤተ ክርቲስያናችን ዋና ጠባቂ አድርጎ የሰየመው ማኅበር እነዚህን መተኪያ የሌላቸው ብርቅየ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት በሕይወት እያሉ ሊደፍራቸው ወይም ቀርቦ ሊያናግራቸው አቅም ሲያንሰው ከሞቱ በኋላ ይወገዙልኝ ብሎ ለሲኖዶስ ስማቸውን ዘርዝሮ እንዳቀረበ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

 

        እናም በክርስቶስ አስታራቂነት ላይ እየተነሳ ላለው ተቃውሞ እኔም እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነቴ የድርሻየን ለማለት የተዘጋጀሁ መሆኑን ስገልጽ ነገር ግን የዚህ ማኅበር አባላት ችግር ከዕውቀትና ከገንዛቤ ማነስ የመጣ ነው ተብሎ በቀላሉ ሊታለፍ የሚገባው አለመሆኑን ላሰምርበት እወዳለሁ። በእልህና በቲፎዞ ብዛት በማምታታት እውነትን ለማስቀየር የሚያደርጉት ውትወታ በዚሁ ከቀጠለ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት አደገኛ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ስለዚህ በዚህ ዘመን ያለን የቤተ ክርስቲያን ልጆች ይህ እንዲሆን አንፈቅድም። የኢንተርኔት ሙግት ለቤተ ክርስቲያናችን የአንድነት ችግር መፍትሔ አያመጣም። ስለዚህ ስለ ክርስቶስ አስታራቂነት በብፁዕ አቡነ በርናባስ በኩል የተላለፈው ትምህርት ስህተት አለበት የሚሉ ካሉ ማስረጃቸውን ይዘው ቀርበው እንዲነጋገሩ ዕድሉ መመቻቸት አለበት። ያ ካልሆነ ግን በስደት የሚኖረው ሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስም አስቸኳይ ስብሰባ አድርጎ በብፁዕ አቡነ በርናባስ ላይ የደረሰውን የስድብ ቃልና በቤተ ክርስቲያናችን ላይም እየተሰረጨ ያለውን የተዛባ አስተምሕሮ አውግዞ መግለጫ ማውጣት ይጠበቅበታል። ለዚህ የተዛባ ትምህርት በመልስ መልክ የተበተኑ ጽሑፎችም ተሰብሰበውና ታርመው በመጽሐፍ መልክ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ሊታደሉ ይገባል ብየ አምናለሁ።

 

የክርስቶስ አስታራቂነት ከቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት አንጻር

የክርስቶስን አስታራቂነት ለመረዳት ሰው የመሆኑን ምሥጢር ማወቅና ጌታ እንደ ሌሎቹ ምሥጢራት ሁሉ ለምልጃም ዓብነት የመሆኑን አስፈላጊነት በጥልቀት መገንዘብ ያስፈልጋል። እነዚህ ሰዎች ምልጃ የሚለውን ቃል የሚፈሩት ለእኔ እስከ ገባኝ ድረስ "አማላጅ" የሚለውን ለቅዱሳን የተሰጠ ጸጋ በባሕርይው አማላክ ለሆነ ጌታ መሥጠት ፍጹም ውርደት መስሎ ስለታያቸው ሊሆን ይችላል። እርሱ ራሱ ሰው መሆኑን አውቆ "ከእኔ አብ ይበልጣል" (ዮሐ 14፡ 28) ብሎ እየመሰከረ ከዚህም ሁሉ በላይ እግዚአብሔር ለእኛ ሲል በለበሰው ሥጋ ሞተ ብለን የምናስተምር ከሆነ አማለደ ብሎ መናገር ለምን እንደሚያስፈራን አይገባኝም።

 

      የክርስቶስን አስታራቂነትን የድኅነትን ምሥጢር በጥልቀት ተረድተናል ብለን አደባባይ ከመውጣታችን በፊት መጻሕፍትን  ከማንበብ ባለፈ በቤተ ክርስቲያናችን መደበኛ ትምህርት ስንት ዓመታትን እንዳሳለፍንና ብሎም ክርስቶስን በሕይወት ለማግኘት እና መንፈሳዊነትን በተግባር ለመለማመድ ምን ያክል ተግተን እንደሠራን ራሳችንን መጠየቅ አለብን። ከሁሉም በላይ ስለ ክርስቶስ አማላጅነት ስንወያይ አማኑኤል ብለን የምንጠራው ጌታ ፍጹም ሰው ፍጹም አማላክ መሆኑንና የእኛን ሥጋ ለብሶ በዓለም ላይ የተገለጠበትንም ዋና ዓላማ ልብ ብሎ ማጤን ያስፈለጋል። ወደ መሠረታዊ ነጥባችን ከመሄዳችን በፊት የሚከተሉትን ጥያቄዎች እናንሳ።

(ሀ) በመሠረቱ ምልጃ ምንድር ነው ለምንስ አስፈለገ?

(ለ) የምልጃ ትምህርት የክርስቶስን ከአምላክነት ክብሩ ዝቅ ያደርገዋል ወይ?

     (ሐ) የክርስቶስ አስታራቂነት ከቅዱሳን ምልጃ በምን ይለያል?

 

(ሀ) ምልጃ ምንድር ነው ለምንስ አስፈለገ?

ምልጃ የተለያዩ አካላትን አስታርቆ አንድ ማድረግ ነው። የምልጃ ሥራ የሚከናወነውም እነዚህ የተለያዩ አካላት አንዱ በደለኛ ሌላው ተበዳይ፣ ወይም አንዱ ኃጢአተኛ ሌላው ጻድቅ ሆነው ሲገኙ በመካከላቸው ያለውን የጥል ግድግዳ አፍርሶ ሁለቱን አንድ ማድረግ ሲያስፈልግ ነው። "እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ…በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ" (ኤፌ 2፡14) ተብሎ የተጻፈለት ክርስቶስ አማላጅ መባሉ ከዚህ አንጻር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። አማላጅ በደለኛው አካል በራሱ ወደ ፈጣሪ መቅረብ ሲያቅተው በእግዚአብሔር ፈቃድ ለኃጢአተኛው የተሰጠ "የመገናኛ ድልድይ" ነው። ለምሳሌ ቴማናዊው ኤልፋዝ እና ጓደኛው ስለ ኃጢአታቸው ተጸጽተው ወደ ፈጣሪ መቅረብ ፈለጉ። ነገር ግን በደላቸው ከለከላቸው። ስለዚህም እግዚአብሔር አለ "እንደ ባሪያዬ እንደ ኢዮብ ቅንን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና ቍጣዬ በአንተና በሁለቱ ባልንጀሮችህ ላይ ነድዶአል። አሁን እንግዲህ ሰባት ወይፈኖችና ሰባት አውራ በጎች ይዛችሁ ወደ ባሪያዬ ወደ ኢዮብ ዘንድ ሂዱ፥ የሚቃጠልንም መሥዋዕት ስለ ራሳችሁ አሳርጉ፤ ባሪያዬም ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልያል፥ እኔም እንደ ስንፍናችሁ እንዳላደርግባችሁ ፊቱን እቀበላለሁ" (ኢዮ 42፡7)።  እንግዲህ ከላይ እንደ ተመለከትነው ከጥንት ዘመን ጀምሮ በተለይ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ የሚደረግ ምልጃ በሁለት መንገዶች ይፈጸማል፦

 

1)   ስለ በደለኛው በመጸለይ  

በአማርኛ ጸሎት የምንለው ቃል በእብራይስጥ "ጣልቃ መግባት" የሚል ፍች ሲኖረው፣ በግሪክኛ ደግሞ "ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር" ወይም "የሰውን ምኞት በእግዚአብሔር ፍላጎት መቀየር" ተብሎ ይተረጎማል። ስለዚህም በደለኛውን ከፈጣሪው ጋር ለማስታረቅና የኃጢአት ሥርየት ለማስገኘት የሚደረግ ጸሎት ወይም ጣልቃ ገብነት ምልጃ ይባላል። እንደ ፈቃዱ የሚደረግ የጸሎት ምልጃ ሁልጊዜም ኃይል አለው። "እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል" (1 ዮሐ 5፡14) ተብሏልና። የግዚአብሔር ፍቃድ ደግሞ የሰው መዳን ነው "በክርስቶስ ለማድረግ እንደ ወደደ እንደ አሳቡ፥ የፈቃዱን ምሥጢር አስታውቆናልና" (ኤፌ 1፡9) ሲል ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው። ምልጃ አንዱ ለሌላው መጸለይ ነው በሚለው ሐሳብ ከተስማማን ክርስቶስም "እኔ ስለ እነዚህ እለምናለሁ" (ዮሐ 17፡9)፤ "ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው" (ዮሐ 17፡11)፤ "አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው" (ሉቃ 23፡24) ብሎ እንደ ጸለየ በቅዱስ መጽሐፍ ተጽፏል።

 

      ክርስቶስ ይቅር ባይ አምላክ ከሆነ ለምን ይቅር በላቸው ብሎ ጸለየ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። በለበሰው ሥጋ በፍቅር ራሱን ዝቅ አድርጎ የአስታራዊነትን ሥራ እየሠራ ነው። ፍጹም ሰው መሆኑን ያመለክታል። የሰው ልጆች ሁላችንም በአዳም አለመታዘዝ ምክንያት በደለኞች በመሆናችን ከመካከላችን ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር ማስታረቅ የሚችል አልተገኘም። እናም በዘር ከሚተላለፍ የውርስ ኃጢአት ነጻ ሆኖ የተገኘ የመጀመሪያው ሰው (ዳግማዊ አዳም) ክርስቶስ በለበሰው ሥጋ ስለ እኛ ማለደ። "በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ፥ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉዝ" (ሮሜ 5፡19) ተብሎ ተንደተጻፈ። አስፈላጊነቱም በእርሱ በኩል የተፈጸመው ሰውን ከእግዚአብሔር ጋራ የማስታረቅ ሥራ በቅዱሳን በኩል እንዲቀጥል ይህን መሠረት ለመጣል ነው። ይህን አስመልክቶ ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስተምር "እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና" በማለት የጌታን አስታራቂነት ከመሰከረ በኋላ ይህ የአስታራቂነት ጸጋ ለቅዱሳን እንደተሰጠ "በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው" (2 ቆሮ 5፡19) ሲል ይመሰክራል።

 

2)የድኅነት መሥዋዕት በማቅረብ

መስዋዕት የሚለው ቃል በእብራይስጥ "መቅረብ" በግሪክኛ ደግሞ "ስጦታ" የሚል ትርጎም አለው። ይህም ሕዝቦች ስለ በደላቸው መስዋዕት በመሰዋትና ለክብሩ የሚገባውን መባ በማዘጋጀት ወደ ፈጣሪ ለመቅረብ ሲፈጽሙት የኖረውን የድኅነት ሥራ የሚገልጽ ነው። የስጦታ መስዋዕት (Offering) እግዚአብሔርን እንደሚያስደስት እርሱ ራሱ "ስጦታ ያመጡልኝ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ተናገር" (ዘፀ 25፡2) ብሎ አዞናልና። ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ መታረቅ ይቀድማል። ሰዎች በሰውነታቸው ዕድፈት ምክንያት የሚያቀርቡት መስዋዕትና የሚሰጡት መባ ዕርቅን ሊያወርድ ባለመቻሉ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ወደ ዓለም በመላክ በልጁ መስዋዕትነት ወደ እርሱ ሊያቀርበን ወደደ። ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ጴጥሮስ በአንድ ቃል እንዲህ ይላሉ። "ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና" (1 ጴጥ 3፡18)። "እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ" (ዕብ 10፡12)።

 

      መስዋዕት በቀጥተኛ ትርጉሙ ስጦታ ነው ካልን ክርስቶስም ስለ ነፍሳችን ዕርቅ ለዓለም ቤዛ ሆኖ የተሰጠ እንከን የሌለበት በግ ነው። "ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘየዓትት ኃጢአተ ዓለም" "እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያርቅ የእግዚአብሔር በግ" (ዮሐ 1፡36) ተብሎ እንደተሳፈ። ቤዛ የሚለው ቃል ከአንድ ዓይነት ግዴታ ወይም ካልተፈለገ ሁኔታ ለማስለቀቅ የሚከፈል ዋጋ ማለት ነው። ስለዚህም በክርስቶስ የደም ዋጋ ተከፍሎልን ከኃጢአት ነጻ መሆናችንን ለመግለጽ "በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም" (1 ቆሮ 6፡19) ይለናል ቅዱስ ጳውሎስ።

 

     በዚህ ሰሞን ምልጃን አስመልክቶ እየተደረገ ያለውን የቃላት ምልልስ ስመለከት ነገሮችን አስተውሎ ካለመረዳት የተነሳ "አንድ ጊዜ ማለደ ይሉና መልሰው ያበዙታል" ብሎ የጻፈ ሞጋች ተመልክቸ ገርሞኛል። በዚህ ጽሑፍ ከመግቢያው ዝቅ ብሎ በተመለከተው አንቀጽ በክርስቶስ የተፈጸመውን የምልጃ ጸሎትና የድኅነት መስዋዕት በአግባቡ ለማስረዳት በ"መገናኛ ድልድይ" መስለነዋል። በዓለመ ሥጋ ያሉ የተራራቁ ሰዎችን ለማገናኘት የሚያስፈልገው  የኢንጅነር ድርሻ የተሰበረውን ድልድይ አንድ ጊዜ መጠገን ወይም መልሶ መሥራት ብቻ ነው። የባለሙያው ድርሻ በዚህ ተጠናቋል። ከዚያ በኋላ ሕዝቦች በመካከላቸው ያለው ግንኙነት ጤናማ እንዲሆን በጋር መሥራትና በፍቅር መኖር የእነርሱ ድርሻ ነው።  

 

      ቅዱሳን ሐዋርያት የክርስቶስን ምልጃ "አንድ ጊዜ" ሲሉ የገለጹት ዕርቅ በክርስቶስ ቤዛነት አንድ ጊዜ በቀራንዮ አደባባይ የተፈጸመ መሆኑን ለማመልከት እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። ከሞት ባሻገር በየዕለቱ ስለእኛ እየወደቀና እየተነሳ ይቃትታል፣ ይማልዳል ወይም ይጸልያል ብሎ ማስተማር ክርስቶስን ዳግም እንደ መስቀል ይቆጠራል። በፕሮቴስታንት እንጅ በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ይህ ዓይነቱ አስተምሕሮ ቦታ የለውም። "እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ፥ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ፥ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል" (ዕብ 9፡28) ብሏል ቅዱስ ጳውሎስ።

 

       ለምሳሌ ጌታ ለእኛ ሲል በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠመቀው ፍዳ በድል ኖሮበት ከኃጢአት ነጻ ለመሆን ፈልጎ አልነበረም። ድኅነተ-ነፍስ የምናገኝበትን ሥርዓት ሊሠራልን ፎልጎ ነው እንጅ። ጥምቀት ዘለዓለማዊ ሥርዓት ነው። በተመሳሳይ መልኩ ስለ ሰው ልጆች ዕርቅ በቀራንዮ አደባባይ ላይ የፈሰሰው ደምና የተቆረሰው ሥጋ ዘለዓለማዊ ሥርዓት ነው (1 ጴጥ 3፡18)። አምላካችን ክርስቶስ ክብር ይግባውና ምልጃን ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው እንድንባቸው ዘንድ የሠራልን የድኅነት ምሥጢራት (Ridemptive Sacraments) ማለትም ምሥጢረ ጥምቀት፣ ንስሐና፣ ቁርባንም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሲፈጸሙ ይኖራሉ። እርሱ ለዘለዓለም ሊቀ ካህናት በመሆኑ ስለ ሰዎች ድኅነት ያቀረበው መስዋዕትና የሠራው ሥርዓትም ለዘለዓለሙ ሥርየት ሲያሰጥ ይኖራል። ስለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ "እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ስለ ተጠራ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው" (ዕብ 5፡9) ሲል የመሰከረው።  

 

       ስለዚህ የክርስቶስ ምልጃ በፍቅር ተገዶ ደካማ ሥጋችንን ተዋሕዶ እኛን ከራሱ ጋር ለማስታረቅ የፈጸመው የቤዛነት ሥራ ነው። ስለ እኛ ራሱን መስዋዕት አድርጎ ስለ አቀረበ "የሐዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት" ተባለ። መስዋዕት ተቀባዩም ራሱ ነው። በዓለም ላይ በሥጋ ቢወሰንም ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ አልተለየምና። ሦስት አካላት ያሉት አንድ አምላክ ራሱን መስዋዕት አድርጎ አዘጋጅቶ ራሱ ሊቀ ካህናት ሆኖ ያቀረበውን መስዋዕት ራሱ ወዶ ፈቅዶ ተቀበለ ማለት በደሙ ኃጢአታችንን አስተሰረየልን ወይም ይቅርታን ሰጥቶ የራሱ ገንዘብ አደረገን ማለት ነው። ይህም በሌላ አነጋገር የወርቅ ቀለበት የጠፋበት ሰው ፈልጎ ካገጀው በኋላ አጥቦና ከቆሻሻው አጽድቶ በጣት ላይ እንደ ማጥለቅና የራስ እንደ ማድረግ ይቆጠራል። ስለዚህ በዚህ መልኩ የተከናወነውን የክርስቶስን አማላጅነት ወይም አስታራቂነት አለመቀበል ድኅነት አልተፈጸመም ከማለት ተለይቶ አይታይም። 

 

      የሦስቱን አካላት እኩልነት አምና በምትቀበል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክርስቶስን ወደ ፍጡራን ተራ ዝቅ የሚያደርግ ትምህርት ቦታ የለውም። በሌላ አነጋገር ስለ አምላክነቱና ስለ ሰውነቱ የተነገሩ ነገሮችን ለይቶ በየፈርጃቸው በማስቀመጥ ፋንታ በአንድ መስመር ለማስኬድ መሞከር አንደገኛ ነው። ለምሳሌ ያስታርቀን ዘንድ በደካማ ሥጋ መገለጡን አስመልክቶ "ከእኔ አብ ይበልጣል" (ዮሐ 14፡ 28)። "አምላኬ አምላኬ ስለ ምን ተውኸኝ" (ማቴ 27፡ 47)፤ "ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዓርጋለሁ" (ዮሐ 20፡ 17) በማለት የተናገራቸውን ቃላት በክርስቶስ መለኮትና ትስብዕት አንድ ሆነዋል በሚል አስተሳሰብ ስለ መለኮትም ጭምር እንደተነገረ የምንጠቅስ ከሆነ ወልድን ከአብ እያሳነስን መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል። ክርስቶስ ሞተልን ስንልም በሥጋው መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ሐዋርያው በግልጽ ቋንቋ "ሞተ በሥጋ ወሃይወ በመንፈስ" "በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ (1 ጴጥ 3፡18) ብሎ እንደመሰከረ።

 

       አንዳንድ የዚህ ትምርህት ተቃዋሚዎች ምልጃ የሚለው ቃል ፈጽሞ ለክርስቶስ ሊሰጥ አይገባም በሚል አቋም   ጸንተው ዕርቅና ምልጃን ሊነጣጥሉ ሲሞክሩ ይስተዋላሉ። እንግዲያውስ የእምነታችን ምስክር የሆኑ ቅዱሳት መጻሕፍት ስለ ክርስቶስ አማላጅነት ምን እንደሚሉ ከዚህ በታች የተሳፉትን ይመልከቱ።

·  ነቢዩ ኢሳይያስ፦ "ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ" (ኢሳ 53፡12)።

·  ሊቁ ቅዱስ ቄርሎስ:- "ወእምድኅረ ኮነ ሰብአ ተሰምየ ብዕሴ ወኢየሱስሃ፣ ወታቦተ ወአራቄ ወበኩረ ለዘሰከቡ" "ሰው ከሆነ በኋላ ብእሲ፥ መሲሕ፥ ኢየሱስ፥ ታቦት፥ አስታራቂ፥ ለሙታን በኩር…ተባለ" (ሃይማኖተ አበው ም 81 ቁ 8 ገጽ 338)።

·  ቅዳሴ ማርያም፦ "አንቃዕደወ ሰማየ ኅበ በቡሁ ወአስተምሐረ ወላዲሁ ወአማኅጸነ አርዳኢሁ ከመ ይዕቀቦሙ እምኩሉ እኩይ" "ወደ ሰማይ ወደ አባቱ ቀና ብሎ አየ፤ ወላጅ አባቱንም ማለደ፤ ደቀ መዛሙርቱንም ከክፉው ሁሉ ይጠብቃቸው ዘንድ አደራ አስጠበቀ" (ቅዳ ማር ቁ 113)።

·  ሊቁ ቅዱስ ቄርሎስ:- "ወሰአሎ ለአብ ያኅልፍ መዐተ ዘረከበነ፣ ከመ ዘለሊሁ ይኄልቁ ስእለተ ሎቱ እስመ ውእቱ ነስአ አምሳሊነ ከም ይስአሎ ለአብ በእንቲአነ" " "እርሱ ለራሱ ልመናን የሚሻ መስሎ ከጥንት ጀምሮ ያገኘንን ፍዳ ከእኛ ያርቅ ዘንድ አብን ማለደው። እንደገና ደግሞ እንዲያስበን ከእርሱም እንዳይለየን ስለእኛ አብን ይማልደው ዘንድ ባሕርያችንን ነስቷልና"  (ሃይ አበ ም 79 ክፍል ቁ 38)።

· ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ:- "እርሱ አንድ ባይሆን ኖሮ የማይሞት ባልሆነም ነበር። የኦሪቱ ካህናት ግን የሚሞቱ ስለሆኑ ብዙ ናቸው። እንደዚሁም ሁሉ ይህ አንድ የሆነው የማይሞት ስለሆነ ነው። ሐዋርያው በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ዘወትር ሊያድናቸው ይችላልና ለዘላለም የማይሞት ሕያው ስለሆነ፤ ስለእነርሱም ይማልድላቸዋል። ወዳጅ ሆይ፤ ይማልድላቸዋል ብሎ ያለው ሰው ስለመሆኑ እንደሆነ ተረዳህን? ሊቀ ካህናት በመሆኑ ያን ጊዜ ይማልድላቸዋል አለ . . . ለዘላለም ሕያው ስለሆነ ለዘወትር ያድናቸው ዘንድ ይችላልና አለ። ከእርሱ በኋላም የሚተካ የለም" (የዮሐንስ አፈወርቅ 13ኛ ድርሳን ቁ 129-131፤ 135-136)።

· ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ:- "እስመ ውእቱ ይተነብል በእንቲአነ" "እርሱ ስለኛ ማልዶልናልና የምናምንበት ሊቀ ካህናት (አስታራቂ) አለው ዮሐ 16፡1-26" (ሃይ አበ ም 63 ክፍል 2 ቁ 26)።

 

   (ለ) የምልጃ ትምህርት ክርስቶስን ከአምላክነት ክብሩ ዝቅ ያደርገዋል ወይ?

ለዚህ ጥያቄ መልሱ አያደርገም የሚል ነው። ለአምላክነት ክብሩ መጨነቃችን አግባብ ነው። ይሁን እንጅ ሥጋ ለብሶ ለቤዛነትና ለዓርአያነት ያከናወናቸው እነዚህ ሥራዎች ከአምላክነት ተራ ዝቅ የሚያደርጉት ሳይሆኑ ፍጹም ፍቅሩንና ትህትናውን የሚገልጹ ናቸው። ይህን ትህትና መሠረት በማድረግ ነው የቅዱሳንን አማላጅነት አምነን የምንቀበለው። ወደ ክርስቶስ በቀጥታ መቅረብ ስንችል የጌታን ቃል በማሰብ በትህትና ቅዱሳንን አማልዱን የምንለው አንዱ ከሌላው በጽድቅ ሥራ የበለጠ መሆኑን በመገንዘብ ነው። "እርስ በርሳችሁ በኃጢአታችሁ ተናዘዙ። ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች" (ያዕቆ 5፡16) ተብሏልና።

 ቅዱስ ጳውሎስ የጌታን ትህትና በሚገርም ቋንቋ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል። "እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፤ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ" (ፊልጵ 1፡6)።

 

         ስለዚህ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ መስዋዕትነት ርቀን የነበረነውን ያቀረበን በመስቀሉም ሰላምን የሰጠን (ኤፌ 2፡16) በመሆኑ አስታራቂነቱን እና ለእኛ ሲል የከፈለውን መከራ ባሰብን ቁጥር የበለጠ እንድንወደውና እንድናከብረው ያደርገናል። የምልጃ ትምህርት ክርስቶስን ከክብሩ ዝቅ ሊያደርገው አይችልም የምንልበት ሌላው ዓቢይ ምክንያት ምልጃ ተቀባይና ዋጋ ሰጭ እርሱ ራሱ በመሆኑ ነው። "ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና" (ዕብ 11፡6) ሲል ቅዱስ ጳውሎስ እንደመሰከረ።

  

 (ሐ) የክርስቶስ አስታራቂነት ከቅዱሳን ምልጃ በምን ይለያል?

የቅዱሳንን ምልጃ ስናስብ ዘወትር ስማቸውን እየጠራን መማጸን የሚኖርብን መሆኑን እንገነዘባለን። ይህንም አውቀን በጸሎት ጊዜ ስማቸውን እየጠራን "አማልደኝ" ወይም "አማልጅኝ" እንላለን። የክርስቶስ አማላጅነት ግን በቀራንዮ አደባባይ በመስቀል ላይ ያለቀ የተጠናቀቀ በመሆኑ "እንደ አምላክነትህ ማረኝ፤ ስለ ፈሰሰው ደምህ ስለ ተቆረሰው ሥጋህ ብለህ ይቅር በለኝ" እንላለን እንጅ አማልደኝ አንልም። ቅዱስ ጳውሎስ "የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ" (ዕብ 9፡12) በሚል ቃል ምልጃ በምድር በለቢሰ ሥጋ የተፈጸመ መሆኑን አረጋግጧል።

 

       የአስታራቂነት ሥራውን አጠናቆ፣ ምርኮን ማርኮ (ኤፌ 4፡8) ወደ ሰማያዊት ድንኳን ወደ ዘለዓለማዊ መንግሥቱ        አርጓል። በአባቱም ቀኝ በክብር ተቀምጧል። ደካማ ሥጋ ከሥጋዊ ባሕርያት ርቆ በመለኮታዊ ክብር ጸንቶ ለዘለዓለም ይኖራል። ከዚህ በኋላ ፈራጅ እንጅ አማላጅ አይደለም። ክብርና መስጋና ለእርሱ ይሁን።

 

የኢትዮጵያ አምላክ ለሁላችንም ማስተዋሉን ያድለን። የቅዱሳን በረከት አይለየን አሜን።

 

ቀሲስ ዘመነ ደስታ

ሳን ሆዜ ካሊፎርንያ