ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን

 

መግቢያ ይህ ጽሑፍ ኦርቶዶክሳዊያን ምዕምናን የሀገራችንንና የቤተ ክርቲያናችንን ወቅታዊ ችግር እንዲገነዘቡ፣ የወደፊት አቅጣጫዋንም መተንበይ እንዲችሉና የመፍትሔውም አካል እንዲሆኑ የቀረበ አጠቃላይ ዳሰሳ ነው። በዳሰሳ መልክ የቀረበው እያንዳንዱ ርዕስ በመረጃ ተተንትኖ ቢጻፍ ራሱን የቻለ መጽሐፍ ሊወጣው እንደሚችል አስቀድሜ ላሰምርበት እወዳለሁ። ይህንንም ጽሑፍ እንዳዘጋጅ የገፋፋኝ በየጊዜው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚፈጸሙ ሕገ-ወጥ ተግባራት መበራከት፣ በየጊዜው የማያቸውና የምሰማቸው ነገሮች ላሳደገችኝ ቤተ ክርስቲያን የሚበጁ አለመሆናቸውን በመገንዘብ ከተማርኩትና ከማውቀው በመነሳት ያለውን ነባራዊ ሁኔታ እውነቱን ላላወቁ ሰዎች በማሳወቅ የድርሻየን መወጣት ብችል የኅሊና ዕረፍትን አገኛለሁ ከሚል ጽኑ እመነት የተነሳ ነው። ስለዚህ ይህ ጽሑፍ በማንም ላይ ያነጣጠረ ሳይሆን የቤተ ክርስቲይናችንንና የሕዝባችን ችግር አጉልቶ የሚያሳይ በመሆኑ በንጹሕ ኅሊና ያንብቡት፤ የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር የልቡናዎትን ዓይን ያብራለዎት፤ አሜን።  

 

በዚህ ዘመን ክርስትናን አዳጋ ላይ ከጣሉት ፈተናዎች መካከል ከውጭ አክራሪ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በክርስቲያኖች ላይ እያደረሱ ያሉት ጥቃት ዋነኛው ሲሆን ከውስጥ ደግሞ ክርስቲያኖች ቤተ ክርስቲያን የምታስተምራቸውን በተፈጥሮ ሕግ ላይ የተመሠረቱ አስተምሕሮዎች ተቀብለው በሥራ ላይ ማዋል መቸገራቸው በዋናነት ይጠቀሳሉ። በተጨማሪም ክርስቲያና ከእውነተኛው የሐዋርያት ትምህርትና የአምልኮት ሥርዓት እየወጣና ዓይነትና መልኩ እየተቀየረ መምጣቱ፣ ክርስቶስን እናመልካለን የሚሉትም ሳያስቡት በሌላ መንፈስ ተጠልፈው በእብደት ጎዳና ላይ መሆናቸው ሌላው የጥፋት ምልክት ነው።  በእርግጥ የአንዳንድ አገሮችና ሕዝቦች ከክርስትና ምርኅ ማፈንገጥ የሚደንቅ አይደለም። ምክንያቱም ክርስትናን በቅርብ ጊዜ በተልዕኮ (በሚሽን) የተቀበሉት በመሆኑ ስር ሰዶ የሕዝቡ ባሕል መሆን አልቻለምና ነው። ኢትዮጵያ ግን ረዥም ታሪክ ያላት ልዩ አገር ናት። ከጥንት ጀምሮ እውነተኛውን አምላክ ከተቀበሉና በቅዱስ መጽሐፍ ስማቸው ከተጠቀሰ ቀደምት አገሮች አንዷ ከመሆኗም በላይ ክርስትናም በኢትዮጵያ ምድር ለ2000 ዓመታት የዘለቀ ታሪክ አለው። ስር ሰዶ የሕዝቡ የዕለት ተዕለት የኑሮ መገለጫ ወይም ባሕል ሆኗል።

 

ይሁን እንጅ አሁን ዘመኑ በእጅጉ ተለውጧል። ወደ ፍጻሜው እየተዳረስን ይመስላል። በዚህ ዘመን የአምላክን ሕልውና የሚክዱ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል። የጋብቻ ክቡርነት ወድቋል፤ መልኩም ተቀይሯል። ፍቅርና አብሮ መኖር ጠፍቷል፤ ብቸኝነት ተስፋፍቷል። የጾታ ግንኙነት (ሴክ) ርካሽ ሆኗል። በጠቅላላው የሰው ልጅ በተፈትሮ ያገኛቸውን ሰብዓዊ ዕሴቶች እየተወና ኅሊና የማይቀበላቸውን ነገሮች በሥራ ላይ እያዋለ ሰይጣንን እስከ ማምለክ ደርሷል። የዚህን ዘመን ፈጣን የጥፋት ጉዞ አስከፊ የሚያደርገው በግልጽ የሚታዩትን ምልክቶች ተመልክቶ የትንቢቱ ፍጻሜ መቃረቡን በመረዳት ትውልዱ እየተጓዘበት ካለው የቅዠት ሕይወት መባነን አለመቻሉ (የሚያስተውል ሰው መጥፋቱ) ነው።  የእነዚህ ነገሮች መስፋፋት በክርስቲያኖች ሕይወት ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ እየበረታ በመምጣቱ የብዙ አብያተ ክርስቲያናት ቀጥተኛ ጉዞ ተደነቃቅፏል፤ መንፈሳዊነታቸውም አዳጋ ውስጥ ወድቋል።

 

በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቀጣይ ሕይዎታቸው አጣብቂኝ ውስጥ ከወደቁ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንዷ ነች። የቤተ ክርስቲያናችን ቀጣይ ሕይወት በአዳጋ ላይ እንዲወድቅ ያደረጉ በርካታ መሠረታዊ ነገሮች ቢኖሩም ለዛሬ በዚህ ጽሐፍ ጥቂቶችን ብቻ እንመለከታለን። ከእነዚህም ዋና ዋናዎቹ፤  

 

(ሀ) የለውጥ ማዕበል ያስከተለው የሞራል ውድቀት (Moral Deterioration)

(ለ) የክህነት ደረጃ ዝቅ ማለትና የምንኩስና ሕይዎት አቅጣጫውን መሳት፣

(ሐ) የዘር ፖለቲካ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያስከተለው ጣጣ፣

(መ) አቅጣጫውን የሳተ የወንጌል ትምህርት፣

 

ሀ) የትውልድ ለውጥ ያስከተለው የሞራል ውድቀት (Moral Deterioration)

ምንም እንኳን የነቁና የሰለጠኑ እየመሰላቸው በዚህ ዘመን የአምላክን ሕልውና የካዱ (Atheist) የሆኑ ወገኖቻችን መኖራቸው የማይካድ ቢሆንም የእግዚአብሔርን ሕልውና አምኖ በመቀበል ኢትዮጵያውያንን የሚቀድማቸው የለም። "የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን? ይላል እግዚአብሔር" (አሞጽ 9፡7) ተብሎ እንደተጻፈ። ነገር ግን የእግዚአብሔርን ሕልውና አምኖ መቀበል ብቻ በራሱ ሃይማኖተኛ አያስብልም። ለምሳሌ አብዛኛዎቹ አውሮፓውያን የፈጣሪን መኖርና የክርስቶስን ሰው መሆን ይቀበላሉ። እንዲያውም በአብዛኛው ክርስቲያኖች ናቸው። የሃይማኖት ሰዎች ግን አይደሉም። እግዚአብሔር በሕይወቴ ውስጥ ቦታ አለው ብሎ መቀበልና ራስን ዝቅ በማድረግ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቆሞ የአምልኮት ተሳታፊ መሆን በእነርሱ ዘንድ የኋላቀርነት ምልክት ከሆነ ሰነባብቷል። በዚህም ምክንያት አለማዊነት (Secularism) ተስፋፍቷል፤ አብያተ ክርስቲያናትም ወደ ሙዜምነት እየተቀየሩ ነው። እነዚህ ክስተቶች የቁሳዊ ፍላጎት ማደግን (Materialism)፣ የሥልጣኔ መስፋፋትንና የቴክኖሎጅ ዕድገትን ተከትሎ የትውልድ ለውጥ (Generational Change) የፈጠራቸው ናቸው። 

 

ይህ ዓይነቱ ለውጥ በኢትዮጵያ መከሰት ከጀመረ የሰነባበተ ቢሆንም የድኅነት መባባስና በአንዲት አገር ሕዝቦች መካከል አንዱ የቴክኖሎጅ ተጠቃሚ ሆኖ በድሎት ሲኖር ሌላው ጦም አዳሪ መሆኑ በድኃና በሀብታም መካከል የተፈጠረው መካካድ ድሀው ፈጣሪውን እንዲያማርርና የምኞት ተገዥ እንዲሆን ሀብታሙም በድሎት ምክንያት ፈጣሪውን እንዲዘነጋ ምክንያት ሆኗል። የሥነ ምግባር ትምህርት (Moral Theology) ምንጭ ቤተ ክርስቲያን ናት። ሰው በድሎት ምክንያት ከቤተ ክርስቲያን ከራቀ ለራሱ ደስ የምያሰኘውን ብቻ እያደረገ መኖር ይጀምራል። አሁን ባለው የኢትዮጵያ መንግሥት በአንድ ወቅት አንድ የፓርላማ አባል ሳያስቡት የእግዚአብሔርን ስም በመጥራታቸው አብዛኛዎቹ የፓርላማ አባላት ምን ያክል እንደሳቁባቸው ይህን ቪዲዮ የተመለከቱ ኢትዮጵያዊያን ሀገራችን በአጉል የሥልጣኔ መንፈስ (Secularism) ከተጠቁና ሃይማኖት ከጠፋባቸው ሀገሮች አንዷ መሆኗን በመገንዘብ ስጋታቸውንና ጸጸታቸውን ሲገልጹ ከርመዋል።

 

ስለዚህም የሰው ልብ ከፊሪሃ እግዚአብሔር የተራቆተ መሆን፣ ለሰው ልጅ ያለን ክብር ዝቅ ማለት፣ የፍቅር ማጣትና የታማኝነት መጉደል በዘምናችን በኢትዮጵያውን ዘንድ የምናስተዋላቸው የትውልድ ለውጥ (Generational Change) የፈጠራቸው የሞራል ዝቅጠቶች ናቸው። ካህናቱም ከዚህ ኅብረተሰብ የተገኙ በመሆናቸው ከላይ ከተጠቀሱት የሥነ-ምግባር ጉድለቶች ነጻ ይሆናሉ ብሎ ማሰብ አይቻልም። ቅዱስ ጳውሎስም ይህን በማሰብ ነው "በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለ ነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጐራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ" (ፊልጵ 2፡14) ሲል የፊልጵስዮስ ክርስቲያኖችን የመከራቸው። አንድ አገልጋይ ካህን ወይም ምዕመን ከነዚህ ዘመን አመጣሽ ወጥመዶች ራሱን ነጻ ማድረግ የሚችለው በሁለት መንገዶ ብቻ ነው።

 

1)   ሲፈጠር ደግ ሆኖ የተፈጠረ ቅን ልቡና ያለው ሰው ከሆነ ብቻ፤ ይህ ዓይነቱ ሰው ወንጌልን በሕይወቱ እየኖረው ሰለሆነ መንፈሳዊ ትምህርት የበለጠ መንፈሳዊ እንዲሆን ይረዳዋል እንጅ በሕይወቱ ውስጥ መሠረታዊ ለውጥ የሚያስፈልገው አይደለም። የዘመኑ የለውጥ ማዕበል አምነቱን ሊፈታተነው ቢሞክርም አይለወጥም። ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ዋጋ የምናገኘው አዘውትረን ወደ ቤተ ክርስቲያን ስለ ማለድን ወይም በአገልግሎት ስለተጋን ሳይሆን በአምላካችን ፊት በቅን ልቡና ስለቀረብን ብቻ ነው። ከዚህ በታች የተመለከተው የቅዱስ ዳዊት ጸሎት በዚህ ዘመን ያለን ክርስቲያኖች ልቡናችንን በየዕለቱ የምንቀተቅጥበት የዘወት መዶሻ ሊሆን ይገባል። "አቤቱ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ…መሥዋዕትን ብትወድድስ በሰጠሁህ ነበር የሚቃጠለውም መሥዋዕት ደስ አያሰኝህም። የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፥ የተሰበርውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም" (መዝ 10፦17)። ከአሕዛብ ወገን ለሆነ ሰው ለቅዱስ ቆርኔሌዎስ መልአከ እግዚአብሔር የተገለጠለት፣ "ጸሎትህና ምጽዋትህ በእግዚአብሔር ፊት ለመታሰቢያ እንዲሆን አረገ" (የሐዋ 10፡4) የተባለለት ብሎም ሳይጠመቅ መንፈስ ቅዱስ የወረደለት በልቡ ንጽሕና ምክንያት ነበር። ይህንም ሰው ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በአምላክ ዘንድ የተወደደ ሲል ገልጾታል (የሐዋ 10፡34)። 

 

2)  ሁለተኛው መንገድ መማር ነው። አንድ ክርስቲያን በደንብ ሲማር፣ የወንጌል ምሥጢርና የክርስቶስ ፍቅር ሲገባው ይለወጣል። በየትኛውም ደረጃ ላይ ያለ ሰው ምንም ያክል በተፈጥሮው ጠማማ ቢሆን አጥብቆ ከተማረና በየዕለቱ የፈጣሪን ቸርነት እያንሰላሰለ ራሱን በጌታ ቃል ከመረመረ ከክፋት ወደ ደግነት መለወጡ የማይቀር ነው። በሌላ አገላለጽ አጥብቆ መማር የሕይወትን መስመር አቅጣጫ የሚያስይዝ ማለትም ለጽድቅ ወይም ለፍርድ የሚያዘጋጅ መለያ መሳሪያ ነው። ብዙ በተማርን ቁጥር የፈጣሪን ቸርነት እየተረዳን ፈሪሃ እግዚአብሔር እያደረብን ይመጣል። በተሰሎንቄ አካባቢ የነበሩ የቤሪያ ሰዎች መጻሕፍትን ብዙ ጊዜ እያነበቡና እየመረመሩ እውነትን ወደ ማወቅ እንደደረሱ ቅዱስ ጳውሎስ ጽፎልናል (የሐዋ 17፡12)። በተቃራኒው ደግሞ አለመማር ለኃጢአት የሚያጋልጥ የጨለማው ሕይወት መሆኑን ጌታ ራሱ "መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ" (ማቴ 22፡29) በማለት ፈሪሳዊያንን የወቀሰበት ትምህርት ለአባባላችን ዓይነተኛ ምሳሌ ይሆነናል። አለመማር ለኃጢአት በር ከፋች የመሆኑን ያህል በተቃራኒው ደግሞ አውቆ እንደሚገባው አለማድረግ ራስን ለበለጠ ፍርድ ማጋለጥ ነው።

 

ችግሩ በአሁን ዘመን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የምናገለግል ካህናትም ሆን ተገልጋይ ምዕመናን ከላይ ከተገለጹት ከሁለቱም ነጻ መሆናችን ነው። የተፈጥሮ ደግነት የሚስተዋልባቸው ወይም በወንጌል ተለውጠው ያገኙት ትህትናና ሰው አክባሪነት የሚታይባቸው ካህናት በጣት የሚቆጠሩ ብቻ ናቸው። ስለዚህ በተፈጥሮው ደግነት የተሰጠው ወይም የሚያስተምረውን በሥራ ላይ የሚያውል የወንጌል ምሥጢር በደንብ የገባው የቤተ ክርስቲያን አባታ እስከሌለ ድረስ በመንጋውና በእረኛው (በመሪውና በተመሪው) መካከል ያለው ልዩነት አንዱ የተካነ ሌላው ጭዋ (ምዕመን) መሆናችን ብቻ ነው ማለት ይቻላል። ሁለታችንም በክርስትና መኖር የተሳነን በመሆናችን በካህናቱና በምዕመናኑ መካከል መከባበር አይሰተዋልም።

 

ካህናቱ ለመሰል ጓደኞቻችን አንታመንም፣ እርስ በራሳችን አንከባበርም፤ መዕመናኑም ይህን አውቀው እኛን በተራ ያዋርዱናል። የለውጥ ማዕበል ያላጠቃቸው ክርስትና የገባቸው በገጠር ያሉ ካህናት ያለ ደመወዝ ሠርተው ራሳቸውን እየረዱ ቤተ ክርስቲያንን በንጽሕና በቅድስና በማገልገል ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ከተማ ቀመስ ካህናት ግን ቤተ ክርስቲያንን የምናገለግለው በእግዚአብሔር ዘንድ በረከትን እናገኛለን ብለን ሳይሆን ለደሞዛችን ስንል ነው። ስለዚህም ለጥቅምና ለሥልጣን ሲባል እርስ በራስ መገፋፋትና አንዱ ሌላውን አሳልፎ መስጠት፣ ወይም ደግሞ ደሞዛችን እንዳይጎድልብን ለእኛ ክብር ለሌላቸው ጭዋ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች ተሽቆጥቁጦና ተለማምጦ መኖር በተለይ በውጭው ዓለም የሚስተዋሉ የተለመዱ ክስተቶች ናቸው።

 

ምእመናኑም አንድ ዓመት ወይም ሁለት ዓመት እየተመላለሰ ሲያገለግል የቆየ ካህን በድንገት ቢሰወር ስልክ ደውለው ምን አገኘህ አባታችን አይሉትም። ለደመውዙ ሲል ነው የሚያገለግለው ብለው ያምናሉና። በተለይም በምንኖርበት በሰሜን አሜሪካ ፕሮቴስታንቶች ከሚያዋርዱን በላይ ኦርቶዶክሳዊያን ምዕመናን በካህናት ላይ የሚያደርሱት በደል በእጅጉ የከፋ ነው። የክህነታቸውን ሥራ የሚያስነቅፍ አስነዋሪ ሥራ ሠርተው ሳይገኙ በቦርድ ከሚያገልግሉበት ቤተ ክርስቲያን የተባረሩ ወይም በላያቸው ላይ የቤተ ክርስቲያን ቁልፍ የተዘጋባቸው ካህናትና ጳጳሳት ቁጥራቸው ብዙ ነው። አንዳንድ ካህናትና ምዕመናን እየሆነ ያለውን ነገር ሲያስቡ ባዶነት ይሰማቸዋል። ኦርቶዶክስን ትተው ወደ ሌላ እምነት ለመፍለስም ይዳዳቸዋል። በአጠቃላይ በዚህ ክፍል የምናየው የአንዱን ወገን ደግነት የሌላውን ክፋት ሳይሆን ሁላችንም በለውጥ ማዕበል የተጠቃን መሆናችንን ነው። ካህኑ የክርስቶስ እንደራሴ መሆኑን ተገንዝቦ ራሱን ከመሰናክል አይጠብቅም (ሮሜ 2፡21)። ምዕመኑም ቄሱ ስለ እርሱ ነፍስ ድኅንነት የሚተጋ የነፍሱ ጠባቂ የቄሱም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብበት ለእርሱ የተሰጠ መሸጋገሪያ ድልድይ ወይም መሰላል መሆኑን አውቆ (ዕብ 13፡17) ካህኑን ያከብርም።

 

ለ) የክህነት ደረጃ ዝቅ ማለትና የምንኩስና ሕይዎት አቅጣጫውን መሳት

ክህነት በእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ በመንፈስ ቅዱስ መራጭነት የሚከናወን መንፈሳዊ ጥሪ ነው እንጅ እንደ ፓርላማ ተወካይ ራሳችንን አጭተን የምናቀርብበት የሚያጓጓ ሹመት አይደለም። በዘመናችን ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችንን አዳጋ ላይ የጣለው የማዕርገ ክህነት ችግር ካህናቱ በለውጥ ማዕበል ከተጠቃና የሞራል ንቅዘት ካገኘው ኅብረተሰብ የተገኘን መሆናችን ሳያንስ፤ የክህነት ማዕርግ በሁለት ምክንያቶች ደረጃው ዝቅ እንዲል ግድ ሆኗል፤

1)  የክህነት መመዘኛ አለመከበርና አገልግሎቱም የመተዳደሪያ ሙያ ሆኖ መቆጠሩ

2) የማዕርገ ክህነት መዛባት በተለይም የምንኩስና ሕይዎት አቅጣጫውን መሳት ዋና ዋናዎቹ ናቸው

 

1)   የክህነት መመዘኛ አለመከበር  

የአንዲት ቤተ ክርስቲያን ጥንካሬ የሚለካው በካህናቶቿ መንፈሳዊ ብርታትና ሥነ-መለኮታዊ ብቃት ነው። እናም በዚህ ክፍል የምናየው የክህነት መመዘኛ አለመከበር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተውሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀጣይ ሕይወት ላይ እያስከተለ ያለው አሉታዊ ተጽዕኖ ይሆናል።  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለአገልግሎት የምንጠቀምበት የትምህርት ዘርፍ ሰፊ በመሆኑ አንድ ግለሰብ ክህነትን ከመቀበሉ በፊት ቢያንስ ለመደበኛ አገልግሎት ብቁ የምያደርገውን የቅዳሴ፣ የዜማና የቅኔ ሙያን ማወቅ ይጠበቅበታል። ያም ባይሆን ከእነዚህ አንዱን ወይም ሁለቱን በከፊል አውቆ በተጨማሪ የሥነ-መለኮትን (Theology) ትምህርት በማጥናት በሚያገለግላት ቤተ ክርስቲያን ለሚነሱ ጥያቄዎች በዶግማም ሆነ በቀኖና ዋና ተጠያቂ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርበታል። ከዚህም በተጨማሪ የሚሰብክና የዘመኑን ሥልጣኔ ተከትሎ ቤተ ክርስቲያንን በአግባቡ ለማስተዳደር ችሎታ ያለው እንዲሆን ያስፈልጋል። ሆኖም አሁን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚስተዋለው እውነታ ከዚህ የተለየ ነው።

 

ቅዳሴን በሲዲ ያጠኑ መደበኛ ትምህርት ያልነካቸው ካህናት ቁጥራቸው ብዙ ነው። የካህናት የሙያ ድክመትና የሞራል ጉድለት የቤተ ክርስቲያንን ውድቀት ያፋጥናል። በተለይም መነኮሳት ሳይማሩ፣ ሳይዘጋጁና በገዳማዊ ሕይወት ሳይፈተኑ በዚህ መንገድ በቀላሉ የቤተ ክርስቲያንን በትረ ሙሴ ለመጨበጥ የሚያደርጉት ሩጫ በቤተ ክርስቲያን ቀጣይ ሕይወት ላይ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት በቀላሉ የሚገመት አይሆንም። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሹመት የሚደረገውን ሩጫ አምርሬ የምነቅፍበት ምክንያት ቴክኖሎጂ በተስፋፋበት ተጠራጣሪና አስቸጋሪ ትውልድ በተፈጠረበት በ21ኛ መቶ ክፍለ ዘመን በአግባቡ ሳይማር በስመ ምንኩስና ለጳጳስነት የበቃ አባት ለቤተ ክርስቲያናችን ሊያበረክት የሚችለው አስተዋጽኦ ውስን በመሆኑ ነው። ከመጀመሪያው የክህነት መመዘኛ መስፈርቱ ወርዶ እንዲህ ዋጋቢስ የሆነበትም ምክንያት ዛሬ የማይቀድሱበትን ክህነት የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ለሌላቸው ወጣቶች በገፍ በመስጠት የክህነትን ማዕርግ በማቃለል ላይ ያሉት ጳጳሳት በተመሳሳይ መንገድ ያለፉና ቤተ ክርስቲያን ወደ የት አቅጣጫ እየተጓዘች እንደሆነ እይታ የሌላቸው በመሆናቸው ነው።

 

በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ የክህነት መመዘኛ መውደቅ የፈጠረው ሌላ ዓቢይ ችግርም አለ። ይህ ዘመን ከእስክድርያ ቤተ ክርስቲያን ተከታታይ የሆነ አባታዊ ጥበቃ በማጣታችንና እንዲሁም የግራኝ መሐመድ ወረራን ተከትሎ ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር በፈጠርነው አግባነት የሌለው ግንኙነት ምክንያት በሥርዓተ አምልኳችን ላይ ሰርገው የገቡ በቀኖና የልተደገፉ ልማዶችን አስወግደን ጥርት ባለ ኦርቶዶክሳዊ ሥርዓት ጸንተን ልንጓዝ የሚገባን ጊዜ ነበር። ሆኖም አንጻራዊ የሥነ-መለኮት ትምህርት (Comparative Technology) ያልተማሩና የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በጥልቀት ያልተረዱ በማኅበር የተደራጁ ሀብታም ወጣቶች በስሜታዊነት ተነሳስተው ራሳቸውን የቤተ ክርስቲያን ተጠያቂ በማድረግ የሊቃውንቱን ጉባኤ በማፈናቸውና በአካበቱት ገንዘብ እያማለሉ ጳጳሳቱንም የራሳቸው ተከታይ በማድረጋቸው ቤተ ክርስቲያኒቱ ወደፊት በመራመድ ፋንታ ሁለትና ሦስት እርምጃ ወደ ኋላ መንደርደር ግድ ሆኖባታል።

 

የክህነትን ክብር ካዋረዱ የቤተ ክርስቲያን ልጆች መካከል የዚህ ማኅበር አባላት በዓይነተኛነት ይጠቀሳሉ። በእነዚህ ወጣቶች ምክንያት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አስተምሕሮን፣ ቀኖናንና መጻሕፍትን መፈተሽ የሚገባው የሊቃውንት ሥራ (Canonization) በአለበት እንዲቆም ግድ ሆኗል። የጻድቃንና የቅዱሳንን ክብር አጉልቶ በመጻፍ ፋንታ የአንዱ ክፍለ ሀገር ጸሐፊ የሌላውን የነቀፈባቸውን ስድብና እርግማን የተሞላባቸው ገድላትና ተአምራት ተሸክመን እየተነቀፍን እንድንኖር ግድ ሆኖብናል። እነዚህ ወጣቶች የቤተ ክርስቲያንን አሥራት በኩራት በመንጠቅና የራሳቸውን መዋቅር በመዘርጋት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማዕከላዊነት እንዳይጠበቅ ማድረጋቸው ሳያንስ ሰርጎ ገብ ልማዶች ይስተካከሉ የሚሉትን ሁሉ "ተሐድሶ" የሚል ስም በመስጠት ሚሊዮኖች ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን እንዲኮበልሉ ምክንያት ሆነዋል። ቤተ ክርስቲያናችን ከአበው ሥርዓት ወጥታ ከእምነት ያፈነገጠን ግለሰብ አስተምሮና አሳምኖ በመመለስ ፋንታ በሌለበት እምነቱን ሳትጠይቅና ሳትመረመር እንድታሳድድና እንድታወግዝ አስገድደዋታል።

 

ይህ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታላቅ ክስረት ነው። ይህ ማኅበር ለአለፉት 25 ዓመታት ሚሊዮኖችን ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በማሳደድ ያተረፈው ቋሚ ነገር የማይነቀል የስም ሐውልት መትከሉ ነው። ይኸውም "ተሐድሶ" የሚለውን ስያሜ ራሱ አውጥቶ ከቤተ ክርስቲያን ያባረራቸውና መድረሻ ያጡ ሰዎች በዚህ ስም እንዲደራጁና የራሳቸውን ተቋም እንዲከፍቱ ማድረጉ ነው። ተሐድሶ የሊቃውንት ማሳደጃ፣ ማኅበሩ የምዕመናን ቀልብ የሚገዛበትና ራሱን የሚያደራጅበት መሣሪያ (ስትራቴጅ) ነው እንጅ የዕመነት ጎራ አይደለም፤ አራት ነጥብ። ተሐድሶ የሚለውን ስም የተቀቡ ጳጳሳት፣ ሊቃውንትና፣ መዘምራን ቁጥራቸው ብዙ ነው። የሚያሳዝነው ግን ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን ገዝግዘው በመጣል ሥርዓት አልባ ለማድረግ የሚያደቡ የፕሮቴስታንት መናፍቃንም ከሊቃውንቱ ጋር እኩል ተሐድሶ መባላቸው ነው። የዚህ ማኅበር አባላት በአሁኑ ጊዜ ተሐድሶ እያሉ የሚከሷቸው ወጣቶች አማራጭ አጥተው ወደ ፕሮቴስታንት ካምፕ የገቡ ሙሉ በሙሉ የሉተርን መርህ የሚከተሉ ናቸው። ተሐድሶ የሚያስብል ከፕሮቴስታንት የተለየ ምንም ዓይነት አመለካከት የላቸውም።

 

በታሪክ በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የምዕመናንን አስራር በኩራት ለራሱ እያስገበረ ቤተ ክህነት የማይቆጣጠረው የራሱ በጀትና የራሱ አስተዳደር አበጅቶ ተመልሶ ቤተ ክርስቲያንን በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ የሚታገል ሃይማኖት ለበስ ድርጅት ይህ ማኅበር ብቻ ነው። በእኔ አመለካከት ይህ ማኅበር አቋሙን ለይቶ ልክ ቢይዝ የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ይለወጣል። በዚህ ሁኔታ ይህ ማኅበር መስመር እንዲገባና የቤተ ክርስቲያን ማዕከላዊነት እንዲጠበቅ ማድረግ ይቻላል የሚባለው ሕልም ግን ለጊዜው የሚታሰብ አይደለም፤ ተአምር ካለተፈጠረ በቀር። ምክንያቱም ጳጳስም ይሁን ቄስ ወይም ዲያቆን አሁን ያለው የኢትዮጵያ ትውልድ ሞራሉ የላሸቀ የለውጥ ማዕበል ያደቀቀው በመሆኑ እንኳን የሃይማኖትህን ክብር እናስጠብቃለን የሚሉትን ይቅርና የሚፈልገውን ጥቅም እስከ አገኘ ድረስ ገዳማት ሲፈርሱ፣ ሴት መነኮሳት ሲደፈሩ ቃል የማይተነፍስ አልፎ ተርፎም ለሚያልፍ ሹመትና ለጊዚያዊ የፖለቲካ ጥቅም ብሎ ወገኑን የሚያጠቃ ኅሊናውን የሸጠ በመሆኑ ነው። ለዚህም "ተሐድሶ" ተብለው በማኅበሩ ልሳን የተወገዙ ጳጳሳትና ካህናት ተመልሰው የማኅበሩ አፈ-ቀላጤ ሆነው አብረው እየሠሩ መሆኑን በማሳየት "ማን ይታመናል?" የሚለው ጥያቄ በእውነትም የዚህ ዘመን የኢትዮጵያዊያን ስጋ መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል።   

 

ብዙዎቹ የዚህ ማኅበር አባላት የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በመደበኛነት ያልተማሩ፣ እንዳይጠይቁም የኮሩ፣ ራሳቸውን የቤተ ክርስቲያን ተጠያቂ አድርገው የሰየሙ፣ እንዲያስተምሩ ፈቃድ የሌላቸው "የጭዋ ሊቃውንት" በመሆናቸው የተሻለ ዕውቀት ያለውን ካህን እንደ ጦር ይፈራሉ። በቤተ ክርስቲያን መድረክ ላይ ቆመው ድፍረት በተሞላበት አንደበት ስድብና እርግማንን የሚዘሩ የሚወዱትን መልአክ የሚጠሉትን ሰይጣን አድርገው የሚሰይሙ የለውጥ ማዕበል የመታው የዘመኑ ትውልድ ዓይነተኛ ነጸብራቅ ናቸው። የሚያሳዝነው ደግሞ በጣም ጥቂትም ቢሆኑ በገንዘብ የሚገዟቸው ነባሩን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የተማሩና በትንሹም ቢሆን በሥነ-መለኮት ትምህርት ያለፉ ካህናቶቻቸውም የጀመርነው አካሄድ ለቤተ ክርስቲያን አይበጅምና እናስተውል ለማለት ወኔ ማጣታቸው ነው።

 

የዚህ ማኅበር አባላት ራሳቸውን የቤተ ክርስቲያን ብቸኛ ተጠያቂ አድርገው ከሰየሙበት ዘመን ጀምሮ ለላፉት 25 ዓመታት በሊቃውንት መካከል ስለ ቤተ ክርስቲያን ተቀራርቦ መወያየት ቅርቷል፤ ፍርሃትና አለመተማመን ተስፋፍቷል። በዕደሜ የገፉ አረጋውያንና በዕውቀት ያልበሰሉ ደካማ ጳጳሳትን እነሱ ያሉትን ሁሉ ትክክል ነው እያሉ ስለሚያንጸባርቁላቸው እኛ ያልነው ሁሉ ትክክል ነው ብለው ያምናሉ። ከዚህም አንጻር ከራሳቸው ቤተ ክርስቲያ አልፈው የእርግማንና የስድብ መርዛቸውን በእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያንም መርጨት ጀምረዋል። በቅርቡ የግብፅ ቤተ ክርስቲያን የእምነት፣ የሥርዓትና የሥነ-ምግባር ጉድለት እንዳለባት አስመስለው ለሲኖዶስ አቅርበው ካወያዩ በኋላ "የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋራ ያላትን የሃይማኖት አንድነት ልትመረምር ነው" በሚል ይህንኑ አሳፋሪ ተግባራቸውን በድኅረ ገጻቸው ይፋ አድርገዋል። ለዚህ ጽሑፍ መልስ "አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ አወጣ" በሚል ርዕሰ በቀሲስ አስተርአየ ሰፊ መልስ የተሰጠ በመሆኑ አንብቦ መረዳት ይጠቅማል።

 

ቤተ ክርስቲያናችን ሥልጣነ ክህነትን በቅዱስ አትናቴዎስ በኩል ከግብፅ ቤተ ክርስቲያን ከተቀበላችበት ጊዜ ጀምሮ 1600 ዓመታት ያህል በእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ስትመራ ቆይታለች። አባቶቻችንም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሚያስትምሩት "አባታችን ማርቆስ እናታችን እስክንድርያ" እያሉ ነው። አሳማ የሚበላ ኦርዶኮሳዊ ቄስ ይኖራል። እኛ አሳማ አንበላም። እሱ አሳማ በመብላት እኛ የኦሪትን ሕግ በመጠበቃችን የባሕል ልዩነታችን እንደተከበረ ይቆያል። በዶግማ፣ በቀኖና እና በጠቅላላ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በኩል ያለን አንድነት ግን ይቀጥላል። የግብፅን ቤተ ክርስቲያን ማንነትና በተለይም የካህናቱ ቅድስና እስከ ምን ድረስ እንደሆነ ዓለም ያወቀው ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እየኖርንና የውስጥ ችግራችንን እያወቅን በሰማዕትነት ጎዳና ላይ ያለችውን "ርትዕት" ቤተ ክርስቲያን መኮነን ያሳፍራል። " መደልው አውጽዕ ቅድመ ሠርዌ እምውሳተ ዓይንከ፤ ወእምዝ ትሬኢ ለአውጽኦ አሠር ዘውስተ ዓይነ እሁከ" "አንተ ግብዝ፥ አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ፥ ከዚያም በኋላ ከወንድምህ ዓይን ጉድፉን ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ" ተብሎ የተጻፈውንም አምላካዊ ቃል እንድናስብ ግድ ይለናል። ለነገሩ ያልገባቸው ወጣቶችን ከኋላቸው አሰልፈው የራሳቸውን አረጋውያን ጳጳሳት ሲያዋርዱና ሲሳደቡ የኖሩ በስሜት የሚንቀሳቀሱና በስም የከበሩ መንፈሳዊያን በመሆናቸው የሌላውን ቤተ ክርስቲያን ካህናት ቢነቅፉ የሚያስደንቅ አይደለም።

 

በሌላ መልኩ በዚህ ማኅበር ግፊት ከግብፅ ቤተ ክርስቲያን ጋር የአስትምህሮ ችግር እንዳለባት እየገለጸች ያለች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ናት እንጅ ከእኛ ጋር የእምነትና የሥርዓት አንድነት ያላቸው ሌሎች አሐት አብያተ ክርስቲያናት ይህን አይሉም። በግብፅ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት መካከልም የአስተምሕሮ ሕጸጽ እንዳለባት የሚያመለክት የእርስ በእርስ መከፋፈል ወይም አለመግባባት ተሰምቶ አያውቅም። በአስተምሕሮም ሆነ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰርገው የገቡ ልማዶን ይስተካከሉ እያሉ የሚጮኹ ሊቃውንትን ማሳደዷን ትታ ውስጧን መፈተሽ ያለባት የእኛ ቤተ ክርስቲያናች ናት።

 

ከዚህ በተቃራኒ ግን ከላይ የተጠቀሰውን ዜና ሳነብ አብሮ የተገለጸ አስገራሚ ነገር ተመልክቻለሁ። ምን አልባትም ተመካክረውበት ሳይሆን የዚህ ማኅበር ጸሐፊዎች ሳያስቡ ያስገቡት ይመስለኛል። ይኸውም በስንክሳራችንና በተአምረ ማርያም ውስጥ ሰው ሠራሽ ግድፈቶች እንዳሉ መጠቀሱ ነው። ሊቃውንቱም ተሐድሶ የተባሉት ይህን የመሰለው አስነቃፊ ነገር ይታረም በማለታቸው ነበር። እኔ እስከ ማውቀው ድረስ ተአምረ ማርያምም አይነበብ ወይም አያስፈልግም ብሎ የተከራከረ የቤተ ክርስቲያን አባት የለም። ሊኖርም አይገባም። ነገር ግን በአንዳንድ ድርሳኖችና በስንክሳራችን ላይ "ሰዎች እንደራሳቸው ስሜት የጻፏቸው ግድፈቶች አሉ" ይስተካከሉ። እነዚህ ስሕተቶች የድርሳኑን ባለቤት (ጻድቅ) እና የቤተ ክርስቲያናችንን ክብር ዝቅ ያደርጋሉ። ድርሳኑም ተቀባይነት እንዳይኖረው ያደርጋሉ ነው የተባለው። እናም አግራሞት የፈጠረብኝ ትላንት በሌሎች አንደበት ሲነገር እንደ መናፍቅነት የተቆጠረ ይህ ሐሳብ ዛሬ ለቤተ ክርስቲያን እንቆረቆራለን በሚሉ ሰዎች ዘንድ ቅዱስ ተግባር ሆኖ ሲነገር መስማቴ ነው።

 

ይህን ጅምር በአውንታዊ ገጽታው እንመለከተዋለን። ሐሳቡንም በደስታም እንቀበላለን። ቤተ ክርስቲያናችን እንዲህ በርቶላት ይህን ማድረግ ከጀመረች በሌሎችም አስተምሕሮዎች ላይ ፍትሻ (Canonization) ልታደርግ ይገባል። ከአሐት አብያተ ክርስቲያናት ጋራ ሊነጥላት ወደ ሚችል አደገኛ ጉዞ መገስገሷን ትታ በቀጥተኛ ኦርቶዶክሳዊ አስትምሕርዋ ላይ ሰርገው የገቡ ኦርቶዶክሳዊ ይዘት የሌላቸው ልማዶችን መፈተሽ፣ እንዲሁም በመዝሙር መሳሪያዎች፣ በሥርዓተ ክህነት፣ በሥርዓተ ምንኩስና፣ በሥርዓተ ፈውስ እና በሌሎችም ሥርዓቶች ላይ ያሉትን ጉድለቶች መርምሮ ቋሚ ሕግ ማውጣት ይገባል። ግብጻውያን አባቶች በተሰጣቸው ጸጋ በጥምቀት ሕሙማንን ይፈውሳሉ። በእኛ ቤተ ክርስቲያን ግን ስውሩ ኃይል ያወጣው ሕግ ይህን ይከለክላል። በሥጋ ወደሙና በቅዱስ ቁርባን ዙሪያም ብዙ የሚያወዛግቡ ነገሮች አሉ። "የራሷ ሲርባት የሰው ታማስላለች" እንዲሉ በውስጧ በልዩነት የተወጠረች ቤተ ክርሲቲያን ሌሎች አሐት አብያተ ክርስቲያናት ስሕተት አላባቸው ማለት ድፍረት ነው። ይህ በዚህ ከቀጠለ ውጤቱ መገንጠል ነው። ከአሐት አብያተ ክርስትያናት የተገነጠለች ብቸኛ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ስያሜዋ ወይም ዕጣዋ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ያስቸግራል።

 

2)የማዕርገ ክህነት መዛባት በተለይም የምንኩስና ሕይዎት አቅጣጫውን መሳት

ይህ ንዑስ ርዕስ ብዙ አወዛጋቢ ነጥቦችን የያዘ በመሆኑ በሰፊ ዝግጅት ወደፊት የመለስበት ሆኖ ለጊዜው አልፈዋለሁ።  

 

(ሐ) የዘር ፖለቲካ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያስከተለው ጣጣ

ኢትዮጵያ ብዙ ብሔር ብሔረሰቦች ተከባብረው የሚኖሩባት ሀገር መሆኗ በቅዱስ መጽሐፍ "በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጉርጉርነቱን ሊለውጥ ይችላልን?" (ኤር 13፡23) ተብሎ ተገልጿል። ይህ ኅብረ-ብሔርነት የጥንካሪያችንና የውበታችን ምልክት ነው እንጅ ለመለያየት ምክንያት ሊሆን አይችልም፤ ሆኖም አያውቅም። ውበት ሆኖ የሚቆጠረው ኅብረ-ብሔርነችን ለጥላቻና ልክፍፍል ምክንያት የሆነው ትውልዱ በለውጥ ማዕበል ከተጠቃ ወዲህ ነው። በቀደመው ርዕሳችን እንደተመለትነው የለውጥ ማዕበል ያጠቃው ትውልድ ከፈጣሪ መንገድና ከበጎ ሥነ-ምግባር የራቀ ብቻ ሳይሆን ጠባብ፣ ራስ ወዳድ፣ የማያምን፣ የማይታመን፣ ትዕግዝት የሌለው፣ ፍቅር የማያውቅ ወገኑን የማያከብር ይሆናል። ለብዙ ዓመታት በጉርብትና አብሮን የኖረ ወገናችን የለውጥ ማዕበል ካጠቃንና ኅሊናችን በጠባብ ስሜት ከተሸረሸረ በኋላ አብሮ አደግ ወንድማችን መሆኑ ቀርቶ ከእኛ ባዕድ የሆነ የሌላ ብሔረሰብ ተወላጅ መሆኑ ይታየናል። መጠኑና ደረጃው ከፍ ወይም ዝቅ ይበል እንጅ በኢትዮጵያ ምድር የዘር ችግር የሌለበት ኢትዮጵያዊ የለም። እንደ ክፉ ካንሰር ወይም እንደ ተዳፈነ እሳት በእያንዳንዳችን ውስጥ ተደብቆ ይኖራል። አንዱን ከአንዱ የሚያበላልጥ የጥቅምና የሹመት ጉዳይ በመጣ ጊዜ ወይም በወንድማማቾች መካከል ጠብን የሚዘራ ክፉ መልእክተኛ ልዩነትን በሰበከ ጊዜ የተደበቀው ክፉ አመል ይፋ ሆኖ ይቀጣጠላል። ጥበበኛው ሰሎሞን   እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች እንዳሉ ከገለጸ በኋላ በወንድማማቾች መካከል መለያየትን የሚዘራን ሰው ነፍሱ አጥብቃ ተጸየፈዋለች ይላል (ምሳሌ 6፡16)።

 

የዘር ልዩነት በፖለቲካና በማኅበራዊ ኑሮ እያደረሰ ካለው ጉዳት በተጨማሪ በሃይማኖት በኩል ያለውን ተጽዕኖ ብንመለከት አንድ ራስ ያላት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በሁለት ፓትርያርክና በሁለት ሲኖዶስ እንድትከፈል ምክንያት ሆኗል። በተለይም በውጭው ዓለም የጎንደር ቤተ ክርስቲያን፣ የሸዋ ቤተ ክርስቲያ፣ የጎጃም ቤተ ክርስቲያ፣ የትግርኛ ተናጋሪዎች ቤተ ክርስቲያ፣ ወዘተ እየተባለ ምዕመናን ከፈለጉት ቤተ ክርስቲያን ሂደው እንዳያስቀድሱ ካህናትም በነጻነት ከፈለጉት ቤተ ክርስቲያን በአገልጋይነት እንዳይመደቡ እንቅፋት በመሆን አንድነታችን እየተፈታተነ ይገኛይል።

 

ዛሬ ዛሬ አንዱ ካህን ሌላውን ካህን የእኛ ሰው ነው ብሎ ለማመንና ወንድሜ ነው ብሎ ለመቀበል ሲሆን ያ ግለሰብ እርሱ ከተወለደበት ወረዳና ቀበሌ የመጣ ያም ባይሆን በክፍለ ሀገር አንድ መሆናቸውን አስቀድሞ ማረጋገጥ አለበት። ይህ የዘር የበላይነትና የእኛነት ስሜት ከጥቅም ፍላጎትና ከሹመት ዓባዜ ጋራ ተጨምሮ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ለሚፈጠሩት ሁከቶች በዋናነት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች አንዱ ነው። የሸዋው ካህን ከጎንደሮች ወይም በተቃራኒው የጎንደር ካህን ከሸዋ ቤተ ክርስቲያን ተመድቦ ማገልገል ከባድ ከሆነ ከእኛ በዘርም ሆነ በቀለም ልዩ የሆነ ነጭ ሰው ቋንቋችንን አጥንቶ አብሮን ሊያገልግልና ክህነት ተቀብሎ ኦርቶዶክስን ሊያስፋፋ ቢፈልግ በምን መልኩ አብረን ልንሠራ እንደምንችል መገመት ከባድ ይመስለኛል። ዘረኝነትና ጠባብ ብሔርተኝነት በዚህ ትውልድ ላይ ይተደነቀረ ካባድ ፈተና ነው። በቤተ ክርስቲያን ዕደገትና በሀገር ሉዓላዊነት ላይ የሚኖረውም አሉታዊ ተጽዕኖ በቀላሉ የሚገመት አይደለም። የአንዲት ሀገር ሰዎች ይልቁንም ክርስቲያኖች ከአንድ አባት ከክርስቶስ በመንፈስ የተወልድን የአንዲት እናት የቤተ ክርስቲያንን የሕይወት ቃል ተመግበን ያደግን መሆንችንን በማሰብ ኅሊናችንን ካልተቆጣጥረን ይህ መንፈስ በጸሎት ጊዜ በግራና በቀኝ አብሮን የቆመውን ሰው በማየት እስከመዘናጋት ድረስ ኅሊናችንን ሊፈታተነን እንደሚችል ልንገነዘብ ይገባል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በቆሮንቶስ ምዕመናን መካከል የነበረውን መለያየት ነቅፎ በጻፈበት መልእክቱ "ክርስቶስ ተከፍሎአልን? ጳውሎስስ ስለ እናንተ ተሰቀለን? ወይስ በጳውሎስ ስም ተጠመቃችሁን?" ሲል የተናገረው ቃል ለእኛ የሚስማማ ትክክለኛ ተግሳጽ ነው ብየ አምናለሁ። ለዘረኝነት በልቡናችን ሰፊ ቦታ ከሰጠነው ወደ ጎጠኝነት እየወረደ በሰፈር እስከ መከፋፈል ሊያደርሰን ይችላል። አንተን ብሎ የመጣውን አብሮህ ሊያገለግል የሚፈልገውን ወንድምህን በዘሩ ምክንያት ገለል የምታደርገው ከሆነ ክርስትናህ ፍጹም አይደለም። መመላለስህም ከንቱ ነው።

 

ክብር ይግባውና መድኃኒታችን ክርስቶስ እናትህና ወንድሞችህ ይፈልጉሀል ተብሎ በተጠየቀ ጊዜ "እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?" በሚል ጥያቄ የመልክተኞችን ሐሳብ ከፈተነ በኋላ "እጁንም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዘርግቶ፦ እነሆ እናቴና ወንድሞቼ" (ማቴ 12፡48) በማለት ከእርሱ ጋራ የሥጋ ተዛምዶ የሌላቸውን ተከታዮቹን ወንድሞቼ ብሎ ሲጠራቸው እንሰማለን። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም ከእስራኤል ዘር ውጭ ትንቢት ካልተነገረላቸው ወገን ለሆነ ለቆርኔሌዎስ ሳይጠመቅ መንፈስ ቅዱስ እንደወረደለትና እግዚአብሔርም ከፍ ከፍ እንዳደረገው ተመልክቶ "እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ…በእውነት አስተዋልሁ" (Act 10:34) ሲል ሰው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እኩል መሆኑን መስክሯል። 

 

(መ) አቅጣጫውን የሳተ የወንጌል ትምህርት

በአሁኑ ዘመን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመቸውም በተሻለ መልኩ በየመደረኩ ሰፊ የወንጌል ትምህርት ይሰጣል። ግቡን ግን አይመታም። ወንጌል ካልተሰበከባቸው ዘመናት ይልቅ ዛሬ ለወንጌል እየተጋን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኦርቶዶክሳዊያንን በመናፍቃን ተነጥቀናል። ለዚህም ዋናው ምክንያት የሚሰበከው ወንጌል አቅጣጫውን የሳተ በመሆኑ ነው።

 

ወንጌላዊነት በአሁኑ ዘመን ሰዎች በንግድ ወይም በሌላ መስመር ያጡትን ጥቅም የሚያስመልሱበት፣ ከልዩ ልዩ የሙያ ክሂሎትና ከፖለቲካ ሹመት ያላገኙትን ክብር የሚያካክሱበት ያልተነቃበት መስመር እየሆነ በመምጣቱ በዓለም ላይ ሰላምን ሊያሰፍንና የተፈለገውንም ውጤት ሊያስገኝ አልቻለም። ለዚህም በተለያየ ሀገር ያሉ የፕሮቴስታንት ፓስተሮች የክርስቲያኖችን ኃብት ሙጥጥ አድርገው በመዘርፍ የናጠጡ ቱጃሮች ከመሆን አልፈው ሰዎች ሳር እንዲበሉና ፓስተራቸውን በጀርባቸው እንዲሸከሙ እስከ ማስገደድ ድረስ በሰው ሕይወት ላይ ምን ያክል እየቀለዱ እንደሆነ ማሳየት በቂ ይመስለኛል።  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን የወንጌል አገልግሎት እስከዚህ ድረስ ወርዷል ለማለት የሚያስደፍር ባይሆንም ለዝነኝነት መሮጥ እና ሌላውን እየኮነኑ ራስን መስበክ የዚህ ዘመን ሁለት መስመር የሳቱ የስብከት ገጽታዎች ናቸው። 

 

አንድ ሰው ምንም ያክል የተናጋሪነት ጸጋ ቢሰጠው ጥሪው ከእግዚአብሔር መሆኑን አረጋግጦ የቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት እንደሚገባው ጥንቅቆ ተምሮና ፈቃድ አግኝቶ ነው ራሱን ከወንጌላውያን ጎራ ማሰለፍ የሚችለው። የተኮነነችን ነፍስ ለማትረፍ እውነተኛውን ጥሪ ተቀብለህ በእውነት የምትንቀሳቀስ ከሆነ ዝነኝነት ሳትፈለገው ይመጣል። ዝነኝነት በረከትን ያስገኛል ተብሎ ባይታመንም።  ጥሪው ከእግዚአብሔር ሳይሆን ዝነኛ በመሆንህ የምታገኘውን ጥቅም እያንሰላሰልክ ሳትማር በልምምድ ታላቅ ሐዋርያ እሆናለሁ ብለህ ብታስብ ግን ከዕውቀትም ከበረከትም የተራቆትህ ሆነህ ትቀራለህ። በሐዋርያት ዘመን የነበረ ዓለምን በሚያስገርም የጥንቁልና ሙያው "ታላቁ የእግዚአብሔር ኃይል" የሚል ቅጽል ስም የተሰጠው ሲሞን የሚባል ሰው የሐዋርያትን ድንቅ ሥራ በመመልከት በጥምቀት ክርስትናን ተቀበሎ ከማኅበረ ክርስቲያን ተቀላቀለ። ነገር ግን የገንዘብና የዝነኝነት ስሜት ከውስጡ ስላልጠፋለት በሐውርያት እጅ መጫን መንፈስ ቅዱስ በሰዎች ላይ ሲወርድ ባየ ጊዜ ይህን ጸጋ በገንዝብ እንዲሸጡለት ሐዋርያትን ለመነ። ምንያቱም ይህን ጸጋ ቢያገኝ ብዙዎችን ሊያስገብራቸውና በአጭሩ ሀብታም ሊሆን እንደሚችል በማሰቡ ነበር። እናም ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ገሰጸው፣ "የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ እንድታገኝ አስበሃልና ብርህ ከአንተ ጋር ይጥፋ። ልብህ በእግዚአብሔር ፊት የቀና አይደለምና ከዚህ ነገር ዕድል ወይም ፈንታ የለህም። እንግዲህ ስለዚህ ክፋትህ ንሰሐ ግባ፥ ምናልባትም የልብህን አሳብ ይቅር ይልህ እንደ ሆነ ወደ እግዚአብሔር ለምን፤ በመራራ መርዝና በዓመፅ እስራት እንዳለህ አይሃለሁና" (የሐዋ 8፡20)። በወንጌል አገልግሎት ለመክበር ለምናስብ ሁሉ ይህ ቃል ትልቅ ማስተንቀቂያ ነው። ለአገልግሎት ሲጠሩ እኔ ዝነኛ ተናጋሪ ነኝና ይህን ያክል ካልተከፈለኝ አልሔድም ማለት ከዚያ አልፎም እንደ ፕሮቴስታንት ወንጌላውያን ስብከትን በሲዲ እያባዙ መሸጥ በእኛ ቤተ ክርስቲያን እየተለመደ የመጣ አደገኛ አዝማሚያ ነው። ፍቅርና መንፈሳዊነት የተለየው በዝነኝነት ላይ የተመሠረተ አገልግሎት በተሰባካያን ሕይወት ላይ ለውጥ የማያመጣ ከመሆን አልፎ በአገልጋዮች መካከል ፉክክርንና ጥላቻን ይወልዳል። በመደጋገፉ ፋንታ አንዱ ሌላውን ማሳደድ ይጀምራል።  

 

ሁለተኛው የተሳሳተ መስመር ስብከታችን ወደ አንድ አቅጣጫ ያዘነበለ እርግማንና ነቀፌታ የተቀላቀለበት መሆኑ ነው። እውነተኛ ወንጌላዊ በፍቅር አስተምሮ ይማርካል እንጅ እየረገመ አያሳድድም። በተቀደሰው መድረክ ላይ ቆሞ አባቶቹን የሚኮንን ሳባኪ በባላቅ እጅ ገንዝብ ተቀብሎ እስራኤል ረግሞ ሊያጠፋ የተላከ በልዓምን ይመስላል። በልዓም አልተሳካለትም። የእግዚአብሔር መልአክ በፊቱ ቆሞ "እነሆ፥ መንገድህ በፊቴ ጠማማ ነውና እቋቋምህ ዘንድ ወጥቼአለሁ" ብሎ ገሰጸው፤ እርግማኑንም ወደ በረከት ቀየረበት፤ በመራገም ፋንታ ባርኮና መርቆ ተመለሰ (ዘኁ 22፡32)። በማውገዝና በማሳደድ የቤተ ክርስቲያን አማኞችን ቁጥር መጨመር አይቻልም። በቁጣና በነቀፌታ እንኳን የፕሮቴስታንት ወጥመድ በተዘረጋበት ቤተ ክርስቲያን ወጣቱን ከመጥፎ ጎድና መታደግ ይቅርና የወልድከውን ልጅ እንኳን ክፉ አመሉን እንዲተው ማድረግ አትችልም።

 

የቤተ ክርስቲያናችን ደካማ የቁጥጥርና የትምህርት ስልት እንኳን እንደተጠበቀችው መላውን አፍሪካን በወንጌል ልታዳርስ ይቅርና የራሷን ምዕመናን መቆጣጠር አላስቻላትም። ለምሳሌ በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነው ኦርቶዶክሳዊያን ነን እያሉ የሚሰብኩትን እና የሚዘምሩትን አገልጋዮች ለማነጋገርና የእምነታቸውን ይዘት መርምሮ መስመር ለማስያዝ በሊቃውንት ጉባኤ በኩል የተውሰደ እርምጃ አለመኖር፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን ውድቀት የሚመኙና ዕድሜ ልካቸውን ሲያደቡ የኖሩ ሉተራዊያን በእጅ አዙር የሚያደርሱትን ተጽዕኖ ለመቋቋም ቤተ ክርስቲያኒቱ በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ ያሉ የሥነ-መለኮትና የፍልስፍና ሊቃውንቶቿን ሰብስባ እንዲወያዩ አለማድረጓና በአጠቃላይም ዓለም አቀፍ ይዘት ያለውን የሥነ-መለኮት ትምህርት አጥንተው ቤተ ክርቲያኒቱን ለማገልገል ዝግጁ ሆነው የሚጠባበቁትን ምሁራንን ገለል በማድረግ በማኅበር ከተደራጁ ጭዋ ምዕምናን ጋር በመጣበቋ ብዙ ሥራ ሊሠራበት የሚችል ወርቃማ ጊዜ በከንቱ እየባከነ ቤተ ክርስቲያኒቱ በየዕለቱ ተከታዮቿን እያጣት ትገኛለች።

 

በዚህ ዘመን ለቤተ ክርስቲያናችን የሚያስፈልጋት በወንጌል ትምህርት የበሰለ፣ የክርስቶስ ፍቅር የገባው፣ በመንፈስ የሚቃጠል፣ በተቀደሰ ሕይወቱ ምሳሌ የሚሆን የንስሐ መምህር ነው እንጅ የራሱን ሰውነት ሳይቆጣጠርና ሥጋዊ አስተሳሰቡን ሳይገዛ በስሜት የሚሮጥ ወንጌላዊ አይደለም። ይህ ዓይነቱን አስተማሪ ቋንቋ እንናገራለን መንፈስ እናስወጣለን እያሉ በሕዝቡ ሕይወት ከሚቀልዱ የፕሮቴስታንት ፓስተሮች ለይቶ ማየት ያስቸግራል። ዛሬ የዘመኑ የለውጥ ማዕበል ላጠቃው ሕዝብ የሚሰጠው ስብከት ራሱን እንዲለውጥ የሚረዳና ለንስሐ የሚያዘጋጅ መሆን ይገባዋል። ሰዎች ተለውጠው መንፈሳዊያን ከሆኑ በኋላ ስለ ቅዱሳን ክብርና አማላጅነት ብንሰብክ ቃሉን በትዕግስት ይቀበላሉ፤ ለማስተማርም ሆነ ስለ እምነታቸው አጥጋቢ መልስ ለመስጠት ብቃት ይኖራቸዋል።

 

በሚገርም መልኩ ላለፉት 25 ዓመታት ከላይ የገለጽኳቸው በማኅበር የተደራጁ ወጣቶች የሚሰብኩት ስብከት አንድ ዓይነት ብቻ ነው። በቅዱሳንን አማላጅነት ላይ ብቻ ያጠነጠነ። በዚህ ሰሞን "ጸረ ተሐድሶ" በሚል መንፈስ በየትኛውም ዓለም እያስተጋቡ ያሉትን ስንመለከት አሁንም ከዚያ መስመር ያልወጡ መሆኑን ያሳያል። በዚህ ወቅት ቤተ ክርስቲያኒቱ አዲስ ችግር ገጥሟት ሕዝቦቿን ለመታደግ ያደረገቸው ወቅታዊ ዘመቻ ይመስላል። ነገር ግን የሰሞኑ አዋጅ የተጠናከረ ከመሆኑ በቀር ለ25 ዓመታት ሲታወጅ የኖረ ነው። የዚህ ማኅበር ሰባክያንን ትምህርት ልብ ብሎ የሚከታተል ሰው የሞተልንን አምላክ የክርስቶስን ክብር ለማወጅና ንስሐን ደፍሮ ለማስተማር ምን ያክል አንደበታቸው የተገታ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።  

 

በዚህም ላይ በየመድረኩ የሚቆሙት ሰባክያን በማሰልጠኛ ያለፉና ፈቃድ የተሰጣቸው ሳይሆኑ አንብበውና ገልብጠው ያንኑ ሲነገር የኖረውን የአማላጅነት ትምህርት መልሰው የሚያስተጋቡ ናቸው። በሥነ-መለኮት ዕውቀት በተለይም በሥጋዌ ትምህርትና በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ላይ ያላቸው ግንዛቤ ጥልቅ ካለመሆኑ የተነሳ "ክርስቶስ በለበሰው ሥጋ ዓለምን አስታረቀ ወይም አማለደ" ተብሎ ሲንገር፣ ወይም የአሳማ ሥጋ መብላት ባህል እንጅ በሃይማኖት መጽሐፋችን የተከለከለ አይደልም ሲባል፤ ወይም ሴቶች በወር አባባቸው ጊዜ ቤተ ክርስቲያን የማይገቡት ስለንጽሕና ነው እንጅ ርኩስ ስለሆኑ አይደለም ተብሎ ሲነገር ሲሰሙ ያዙኝ ልቀቁኝ ይላሉ። መጠየቅ ግን አይፈልጉም፤ እንኳን ለማስረዳት ለመረዳት ችሎታ የላቸውምና። እናም በመጠየቅ ፋንታ በአባቶች ላይ የስድብ ውርጅብኝ ያወርዳሉ። በማኅበሩ ተልከው በእነ ቅዱስ ጴጥሮስ መድረክ ላይ በድፍረት ቢቆሙም በስሜት የሚንተገተጉ ተናጋሪዎች ናቸው እንጅ መንፈሳዊያን አይደሉም። ምክንያቱም መንፈሳዊ ሰው ወንጌል ጨብጦ አባቶቹን አይራገምምና ነው። ስሜታዊና ተሳዳቢ ሰባኪ ሰይፍ የሚመዝ ጦረኛ ትውልድን ይፈጥራል። በክርስትና የተሰጠን ትዕዛዝ "ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ፥ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋልና" (1 ጴጥ 3፡9)። "የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር፦ ጌታ ይገሥጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም" (ይሁዳ 1፡9) የሚል ነው።

 

እርግጥ ነው "በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን" (1 ጴጥ 3፡15) በተባለው መሠረት ኦርቶዶክሳዊ አስተምሕሮን ለሚክዱ መናፍቃን ተዘጋጅቶ መልስ መስጠት ይገባል። ነገር ግን በየዓውደ ምሕረቱ ተመሳሳይ ትምህርት ለበርካታ ዓመታት ማስተጋባት ጦረኛ ያስብላል፤ የምዕመናንንም ጆሮ ያደነቁራል። ለውጥም አያመጣም።

 

ማጠቃለያ

ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ጥርት ባለ ኦርቶዶክሳዊ አስተምሕሮና ጥርት ባለ ኦርቶዶክሳዊ ሥርዓት ጸንታ ትኖር ዘንድ በዚህ ወቅት ቀኖናዊ ፍተሻ (Canonization) ማካሔድ ያስፈልጋል። ህይንንም ለማድረግ የሊቃውንት ጉባኤ ከማንም ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆኖ ሥራውን ማከናውን ይኖርበታል። የከተማ ብሕትውና፣ የምንኩስና ሕይወት፣ የጥምቀትና የፈውስ ሥርዓት መስመር መያዝ ዓለበት። የካህናት የሙያ ድክመትና የሞራል ጉድለት የቤተ ክርስቲያንን ውድቀት ያፋጥናል። ስለዚህ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሲኖዶስ የክህነትን መመዘኛ እንዲያስጠብቅ፣ ግልጽ የሆነ የሥነ-ምግባር ችግር ያለባቸው ካህናት ቤተ ክርስቲያንን ተጣብቀው ክርስትናን ከሚያስነቅፉ በራሳቸው ሠርተው እንዲተዳደሩ እንዲደረግ በአጠቃላይም በክርስትና ሃይማኖት ስም ማምታታት እንዲቆም በጩኸትና በስድብ ሳይሆን ቀረብ ብሎ አባቶችን በማወያየት የድርሻችንን መወጣት እንዳለብም መገንዘብ ያስፈልጋል።

 

ሕዝባችን በለውጥ ማዕበል ተመቶ ከፍተኛ የሆነ የሞራል ውድቀት ገጥሞታል። ኦርቶዶክሳዊ ክርስትናችንም አዳጋ ተጋርጦበታል። ንስሐ የሚገባ ሰው የለም። ሥጋውና ደሙን የሚቀበለው ኦርቶዶክሳዊ ቁጥር እጅግ በጣም ውስን ነው። ቀዳሽና አስቀዳሽ ሰባኪና ተሰባኪ በተመሳሳይ መንፈሳዊ ይዘት ባሉበት በዚህ ዘመን ይህን የለውጥ ማዕበል መግታትና የሕዝቡን ልብ መቀየር ከባድ ሊሆን ይችላል። እናም መፍትሔው "አቤቱ ሕዝብህን አድን ርስትህንም ባርክ" እያሉ መጸለይና ከዚህም ጋር የስብከታችንን መስመር ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ በማስተካከል በየዕለቱ ንስሐን ማወጅ ነው።

  

ይህም ማኅበር ነጠላ ለብሶ ፍጹም ክርስቲያን በመምሰል የቤተ ክርቲያናችንን በር ዘግቶ ምዕመናንን እና ካህናትን ማሳደዱን እንዲያቆም፤ በሰበካ ጉባኤ፣ በሰንበት ትምህርት ቤት፣ በአስተዳደር፣ በሊቃውንት ጉባኤ እና በሁሉም ዘርፍ እጁን እያስገባ ማበጣበጡን እንዲተው፤ የቤተ ክርስቲያን አባቶችን አረጋዊያን ሊቃነ ጳጳሳትን ለተሳደበበት ኃጢአቱ ንስሐ እንዲገባ መምከር ያስፈልጋል። ገንዘብ ስላለን ቤተ ክርስቲያኒቱን እኛ ባለምነው መስመር እናስኬዳለን ወይም እኛ የተከተልነው መስመር ብቻ ለቤተ ክርስቲያን ቀጣይ ሕይወት ብቸኛ አማረጭ ነው ብሎ ማሰብ አላዋቂነት ነው። በነባሩ ትምህርት (በቆሎ ትምህርት ቤት) በሥነ-መለኮትና በፍልስፍና ጥበብ የተካኑ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቀጥተኛ አስተምሕሮና እውነተኛ ሥርዓት የት ላይ እንደሆነ አነጻጽረው የተማሩ ኢትዮጵያዊያን ሊቃውንት ቁጥራቸው በጣም ብዙ ነው። ማኅበሩ ለኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በትክክል የሚያስብ ከሆነ ከሌሎች ጋራ አብሮ ለመሥራት ፈቃደኛ መሆን አለበት።

 

የኢትዮጵያ አምላክ ለሁላችንም ማስተዋሉን ያድለን። የቅዱሳን በረከት አይለየን አሜን።

 

ቀሲስ ዘመነ ደስታ

ሳን ሆዜ ካሊፎርንያ