መናፍቅነት በቤተ ክርስቲያን ታሪክ

የመገንጠል አዝማሚያ ያላቸው የመናፍቃን ባሕርያት በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን

Sectarian Mind-Set within the Realm of Orthodoxy

 

በአለንበት ዘመን አንዱ ከምንም ተነስቶ ባልገባው ነገር በአንዱ ላይ "መናፍቅ" የሚል ቅጽል መለጠፍና ማሸማቀቅ የተለመደ ተገባር እየሆነ መጥቷል። በተቃራኒው ደግሞ ወንጌላዊነትን ለዝነኝነትና በዚሁም ሰበብ ለገንዘብ መሰብሰቢያ መጠቀሚያ በማድረግ በመዝሙርም ሆነ በትምህርት ከተለመደው ወጣ ባለ ሁኔታ በራሳቸው የልብ ወልድ መንገድ የሚጓዙ ቁጥራቸው ጥቂት አይደለም። አንድን ግለሰብ ወይም ቡድን መናፍቅ ወይም ተገንጣይ የሚያስብለው የሚሰጠው የወንጌል ትምህርት ከእውነተኛው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ የተለየ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን ራስን "ከቤተ ክርስቲያን አንድነት ለመገንጠል ባለው አዝማሚያ" (Schismatism, Sectarianism) ጭምር እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል። በረዥሙ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የመገንጠል አዝማማያ የነበራቸውና ያላቸው የመናፍቃን ባሕርያት ምን እንደሚመስል ጥቂቶችን ብቻ ቀጥሎ እንመለከታለን። ታሪክ ራሱን ይደግማል እንዲሉ ይህ ዓይነቱ ተግባር ዛሬም እየተፈጸመ በመሆኑ እነዚህን መስፈርቶች ተመልክቶ ነው ሰውን ከዝንባሌውና ከተግባሩ አንጻር መናፍቅ ወይም ተገንጣይ ማለት የሚቻለው።  

 

(1)  ሌላውን አጥብቀው እየኮነኑ ራሳቸውን በፍጹምነት ደረጃ ያስቀመጡ ወይም ራሳቸውን የጻድቃን ማኅበር ብለው የሰየሙ። ፍጹም አክራሪዎች (Excessive Rigorism) ማለትም የማይጾሙትንና የማይጸልዩትን በፍቅር በማስተማር ፋንታ የጠፉ አድርገው የሚቆጥሩ፣ ከራሳቸው እምነት ውጭ ባሉ የእምነት ተቋማት ላይ ፍጹም ሆነ ጥላቻ ያደረባቸውና ከእነርሱ ጋር በምንም ዓይነት መንገድ መተባበርን እንደ መርከስ አድርገው የሚቆጥሩ ናቸው።

ምሳሌ፦

·  በ2ኛው መቶ ክ/ዘመን በሶርያና በአካባቢው የነበረ ተርቱሊያን (155 - c. 240 A.D) የተባለ የቤተ ክርስቲያን አባት እና በእርሱ የሚመራ ሞንታኒስት የሚባል ቡድን፣ በኤስያና በሮም አካባቢ የነበሩ ንጹሐን የተባሉ  ኖቬሺኒስቶች፣ እንዲሁም በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን በምሥራቅ አፍሪካ የነበሩ ዶናቲስቶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው። እነዚህ ቡድኖች ራሳቸውን "መንፈስ ቅዱስ የሞላብን የጻድቃን ማኅበር ነን" ብለው ከመሰየማቸውም በላይ ኃጢአት የሠሩ ወይም በዘመነ ሰማዕታት መከራ ፈርተው እምነታቸውን የለወጡ ክርስቲያኖች በንስሐ እንዳይመለሱ እንቅፋት በመፍጠር የቤተ ክርስቲያንን ቀጥተኛ ጉዞ በማደናቀፋቸው ከቤተ ክርስቲያን አንድነት ተወግዘው ተለይተዋል። በተለይም ዶናቲስቶች የምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አፈጻጸም (ፍጹምነት) የሚወሰነው በካህኑ ንጽሕናና ቅድስና ነው በሚል የተሳሳተ ትምህርታቸው ይታወቃሉ።   

(2) የወንጌልን ትምህርትና የክርስቶስን በጎ ፈቃድ በጥልቀት ካለመረዳት የተነሳ የተጻፉ ነገሮችን በራሳቸው አባባል ተርጉመው በራሳቸው መንገድ የሚሄዱ፤ እነሱ ትክክል ነው ብለው ያመኑትን ነገር የማይቀበለውን አጥብቀው የሚኮንኑ። ምሳሌ፦

·  በሁለተኛው መቶ ዘመን የነበረ ታትያን የተባለ የቤተ ክርስቲያን አባት የሚመራቸው እንክራቲስትስ የተባሉ ቡድኖች ለዚህ በአብነት ይጠቀሳሉ። የዚህ ቡድን አባላት ራሳቸችንን መቆጣጠር የምንችል "ተሐራምያን" ነን ብለው የሚያስቡ ሲሆን ጋብቻና ሥጋ መብላትን አጥብቀው ይጸየፉ ነበር። በዚህም ትምህርታቸው ከቤተ ክርስቲያን ተወግዘው ተለይተዋል።

(3) በዚህ ዓለም የሰው ልጆች በሚፈጽሟቸው ነገሮች ላይ አሉታዊ (ነጋቲብ) አመለካከት ያላቸውና ብሎም ዓለምንና በውስጧ ያለውን ነገር ሁሉ በጥላቻ የሚመለከቱ። እንዲሁም የዚህን ዓለም ኅልፈት አበክረው በመስበክ ሰውን የሚያዘናጉ። (ማሳሌ ከላይ የጠቀናቸው ታትያንና ተርቱሊያን)።

ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ "የጌታ ቀን ደርሶአል ብላችሁ፥ ከአእምሮአችሁ ቶሎ እንዳትናወጡ….ማንም በማናቸውም መንገድ አያስታችሁ" ሲል ይመክረናል (2 ተሰ 2፡3)።

(4) ለአባቶች የማይታዘዙ፣ ሁሉን በእኩልነት የማየት ችግር ያለባቸውና ፍቅር የጎደላቸው፤ ከአሳደገቻቸው ቤተ ክርስቲያን ፍቅር ይልቅ ጓደኛዊ ቡድንተኝነት የሚያሸንፋቸው ናቸው።

ምሳሌ፦

·  በራሻ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የአሮጌው ሥርዓት ተከታዮች በምሳሌነት ይጠቀሳሉ። እነዚህ ቡድኖች የራሻ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከ1666-1667 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በቅዳሴዋ ላይ ቀኖናዊ ማስተካከያ በማድረጓ ይኸን ተቃውመው ራሳቸውን ከቤተ ክርስቲያን አንድነት የገነጠሉ ቡድኖች ናቸው።

·  በግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የአሮጌው ካላንደር ተከያዮች በሁለተኛነት ይጠቀሳሉ። እነዚህ ቡድኖች በ1923 ዓ.ም የግሪጎርያን ካሌንደር ለምን ማስተካከያ ተደረገበት ብለው በመቃወምና በተጨማሪም የግሪክ ቤተ ክርስቲያን ከሁሉም የተለየችና የከበረች ስለሆነች ከዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ መሳተፍ የለባትም በሚል ተቃውመው ራሳቸውን የገነጠሉ ናቸው። በኦርቶዶክስና በካቶሊክ ሕግ የአንዲት ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያንን ዶግማ ሳይነካ ሥርአቷን በቀኖና የማስተካከል ሥልጣን እንዳለው ሊታወቅ ይገባል።

(5) አባቶቻቸው ጠብቀው ላቆዩት ታሪክ ግድ የሌላቸው፤ የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን የዶግማ አስተምሕሮና በቀኖና የተደገፈ ሥርዓቷን አጥብቆ በመኮነን ትክክለኛ ነው የሚሉትን በራሳቸው መንገድ የሚያስተምሩ፤ የግል ተደማጭነትንና ተወዳጅነትን እንዲሁም የፖለቲካን ክብርና የገንዘብ ጥቅምን ከሃይማኖት በላይ አድርጎ አድርገው የሚመለከቱ ቡድኖች ናቸው። የዚህ ዓይነት አመለካከት ያላቸው ቡድኖች እልኸኞች ናቸው። እኛ የያዝነው እውነት ለሌሎች አልተገለጠላቸውም ብለው ያምናሉ እንጅ በተሳሳተ መንገድ እየሄዱ መሆናቸውን አይገነዘቡም።

ምሳሌ፦ ከ16ኛው መቶ ክ/ዘመን ጀምሮ መቋጫ በሌለው የመከፋፈል ሂደት ላይ የሚገኙ የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት፣ በኦርቶድክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥም ሆነው አመለካከታቸውን ሊጥሉ ያልቻሉ ራስ ተፈሪያን እና እንዲሁም በቅርቡ ራሳቸውን ተሐድሶ ነን ብለው ይፋ ያደረጉ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በዋናነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።

 

ማጠቃለያ ምክር፦ የቤተ ክርስቲያናችን ካህናትም ሆኑ ወንጌላውያን ግለሰቦች ናቸውና ሊሳሳቱ ይችላሉ። እውነተኛውን የኦርቶዶክስ ትምህርት ሲያስተምሩ የምስጋና መዝሙር የምንዘምርላቸውን ያህል ሲሳቱም በልጅነት ልንመክራቸው ይገባል እንጅ የሄዱበት መስመር የተሳሳተ መሆኑን እያወቅን ግለሰቦችን ተከትሎ ቤተ ክርስቲያን መካድ እጅግ የሚያሳፍር ነው። ውድ ኦርቶዶክሳዊያን!! "እውነት አንዲት ብቻ ናት"፤ ሁለት ወይም ሦስት ልትሆን አትችልም። በእምነትና በሥርዓተ-ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚነሱ ውዝግቦች መስመር ሊይዙ የሚችለው ከእልኸኝነት በጸዳ መንፈስ መነጋገርና መደማመጥ ሲቻል ነው። መነጋገርና መደማመጥ ይቻል ዘንድ በቤተ ክርስቲያን ትምህርት ቤት ያላለፉ ምዕመናን በግራና በቀኝ ሆነው ነገሮችን ከማራገብ ተቆጥበው አደብ ሊገዙ ይገባል። ሐሰት በደጋፊ ብዛት እውነት ሊሆን አይችልምና። ብዙ የወንጌል መልእክቶች በየደቂቃው ፌስ ቡክ ላይ ይለጠፋሉ። ምዕመናኑም እየተቀበሉ በየሰከንዱ "ቃለ ሕይወት ያሰማልን!" ይላሉ። መልካም ነው!! በአንድ በኩል ስለ ቃሉ ያለንን ክብር መግለጣችን በጣም ደስ ይላል። በሌላ በኩል ግን የተላለፈው መልእከት ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሯችንን የጠበቀ ትክክለኛ ትምህርት መሆኑን አረጋግጠው መመስከር የሚችሉ የትኞቹ እንደሆኑ ማወቅ አይቻልም። ስለዚህ አደብ ካልገዛን የአንድ ወገን ደጋፊ በመሆን በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ሊፈጠር ለሚችለው መከፋፈል (Schism) ምክንያት ልንሆን እንደምንችል ተገንዝበን ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል።

 

የቤተ ክርስቲያን አምላክ ይጠብቀን

የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ጸጋና በረከት አይለየን፤ አሜን።

 

ቀሲስ ዘመነ ደስታ

ሳን ሆዜ ካሊፎርንያ